የአእዋፋቱ ንጉሥ
South African Folktale
Wiehan de Jager

ከረጅም ጊዜ በፊት፣ አእዋፍ ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ ልክ እንደ ሰዎች እና እንደ እንስሳት እነሱም ንጉሥ ይፈልጋሉ፡፡ የትኛው የአእዋፍ ዘርያ ንጉሥ ይሁን?

1

አንዲት ወፍ "ንስር፣ እሱ ጠንካራ እና ንጉሣዊ ነው!" አለች፡፡ "አይሆንም፣ እሱ ዘውድ የለውም እና ሲጣራም ድምፁ በጣም አስከፊ ነው" በማለት ሌላዋ ተቃወመች፡፡ አንዱ "እንግዳውስ ግዙፍ እና እንደ አንበሳ የሚያገሳ ስለሆነ ሰጎን ይሁን" አለ፡፡ "አይ እሱ መብረር አይችልም፡፡ የአእዋፍ ንጉሥ ደግሞ መብረር መቻል አለበት፡፡"

2

ፒኮክ "እኔ ንጉሥ መሆን አለብኝ ብዬ አስባለሁ" አለ፡፡ ረጅም ጭራውን እየዘረጋጋ "እኔ በጣም ቆንጆ ነኝ"፡፡ ጉጉት "አንተ በጣም ትኩራራለህ" አለው፡፡ "እኔ ከማንኛውም ወፍ የበለጠ ትልቅ ዓይን አለኝ፡፡ ንጉሥ መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ" አለ፡፡ ሌሎች ወፎች "አይ ጉጉት አንተ አትሆንም ፡፡ ፀሐይ ሲወጣ እኮ ልተተኛ ትሄዳለህ" ሲሉ ተንጫጩ፡፡

3

እናም ንጉሥ ለመምረጥ እየተቃረቡ ነው፡፡ ከዚያም አንዲት ወፍ "ከሁሉም የበለጠ በከፍታ መብረር የሚችል ንጉሥ መሆን አለበት" ብላ አንድ ሐሳብ አቀረበች፡፡ ሁሉም አእወፍ "አዎ! አዎ!" እያሉ በመጮኽ ወደ ሰማይ ከፍ፣ ከፍ እያሉ በረሩ፡፡

4

ዝይ በዓለም ከፍተኛው ከሆነው ተራራ በላይ እስከ ምትደርስ ለአንድ ቀን በረረች፡፡ ንስር ከሁሉም ተራራዎች በላይ ለሁለት ቀናት ወደ ሰማይ በረረ፡፡ ቢሆንም ጥንብ አንሳ ሳያቋርጥ ለሦስት ሙሉ ቀናት ወደ ፀሐይ አቅጣጫ በሯል፡፡ ጥንብ አንሳ ከሁሉም በላይ እርቆ "እኔ የበላይ ነኝ፣ እኔ ንጉሥ ነኝ!" ሲል ሁሉም አእዋፍ ሰምቶታል፡፡

5

ነገር ግን ጥንብ አንሣ "ጥንብ አንሣ! ጥንብ አንሣ! ጥንብ አንሣ! እኔ ነኝ የበላይ፣ እኔ ነኝ ንጉሥ" የሚል ድምጽ ከበላዩ ሰማ፡፡ ይህን ያለው ከሁሉም ወፎች ትንሽ የሆነው ድንቢጥ ነበር፡፡ ጥንብ አንሣም ትላልቅ ክንፎቹን እያራገበ ወደ ሰማይ ከፍ ብሎ በረረ፡፡

6

"ድጋሜ አታሸንፈኝም" አለ እና ጥንብ አንሣ አየሩን እየቀዘፈ ቀጥታ ወደላይ በረረ፡፡ አቅሙ እስከ ቻለ ድረስ ከፍ፣ ከፍ እያለ በረረ፡፡ "እኔ ከማኝኛውም ወፍ በላይ ነኝ፡፡ ንጉሣችሁ እኔ ነኝ!" እያለ ተነጫነጨ፡፡

7

ነገር ግን ትንሹ ወፍ ድንቢጥ ከጥንብ አንሣው ክንፍ ወደላይ ከፍ አለ፡፡ "ጥንብ አንሣ! ጥንብ አንሣ! ጥንብ አንሣ! ጥንብ አንሣ! እኔ ነኝ የበላይ፣ እኔ ነኝ፤ እጅግ በጣም ትንሹ ወፍ! ንጉሣችሁ ነኝ" አለ፡፡ ጥንብ አንሣ እርቆ ለመብረር በጣም ደክሞት ነበር፡፡

8

ጥንብ አንሣ ወደታች ተመለሰ፤ አሁንም ትንሹ ወፍ ከጥንብ አንሣው ክንፍ ብዙም አልራቀም፡፡ ሌሎች ወፎች በድንቢጥ ማሸነፍ በጣም ተናደዋል፡፡ ላባውን በሙሉ ለመነቃቀልም ተዘጋጅተዋል፡፡

9

ነገር ግን ድንቢጥ ሁሉም ወፎች ምን ያህል እንደተናደዱ ስላየ ወደ እባብ ጉድጓድ ፈጠን ብሎ ገባ፡፡ እየጠበቁት ያሉት ወፎችም ለጉጉት "በትላልቅ ዓይኖችህ ተከታትለህ፣ ከጉድጓዱ ሲወጣ መያዝ አለብህ" አሉት፡፡ ለዚያም ጉጉት ከጉድጓዱ ፊት ለፊት ተቀመጠ፡፡

10

ቢሆንም ፀሐይ ስለሞቀ ጉጉትን ወዲያው እንቅልፍ ያዘው፡፡ ትንሹ ድንቢጥ ከእባቡ ጉድጓድ ወጣ፡፡ ሲመለከት ጉጉት ተኝቷል፤ ወደ ላይ በረረ እና አመለጠ፡፡

11

ጉጉት ትንሹን ወፍ በማስመለጡ ሃፍረት ተሰማው፡፡ አሁን ማታ ማታ ብቻ እየወጣ ያድናል፡፡ ቀን ላይ ከሌሎቹ ወፎች እይታ እርቆ ተኝቶ ይውላል፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
የአእዋፋቱ ንጉሥ
Author - South African Folktale
Translation - Kebede Yimer
Illustration - Wiehan de Jager
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs