ጉጉ ግልገል ዝኆን
Judith Baker
Wiehan de Jager

ዝኆን በጣም ረዥም አፍንጫ እንዳለው ሁሉም ሰው ያውቃል።

1

ይሁን እንጂ ከረጅም ጊዜ በፊት የዝኆን አፍንጫ አጭር እና ሰፊ ነበር፡፡ ልክ ፊቱ መሀል ላይ ጫማ ያለበት ያስመስለው ነበር።

2

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ዝኆን ተወለደች፡፡ ስለ ሁሉም ነገር የማወቅ ጉጉት ነበረባት። እያንዳንዱን እንስሳ አንድ አንድ ጥያቄ ትጠይቅ ነበር፡፡

3

ስለ ቀጭኔ የማወቅ ጉጉት አድሮባት ነበር። ‹‹ለምን ረዥም አንገት ኖረሽ?›› ብላ ጠየቀቻት፡፡

4

ስለ አውራሪስ የማወቅ ጉጉት አድሮባት ነበር። ‹‹ቀንድህ ለምን ስለታም ሆነ?››

5

ስለ ጉማሬ ለማወቅ ትጓጓ ነበር፡፡ ‹‹ለምን ቀይ ዓይኖች ኖሩሽ?›› በማለት ጠየቀቻት፡፡

6

ስለ አዞ ለማወቅ በጣም ትጓጓ ነበር፡፡ ‹‹አዞ ለእራት ምን ይበላል?›› ብላ ጠየቀች፡፡

7

‹‹እንደዚህ ያለ ጥያቄ በጭራሽ አትጠይቂ!›› አለቻት እናቷ፡፡ እሷም ተናዳ እየተኮሳተረች ወጣች፡፡

8

ቁራ በፍጥነት ወደ ግልገሏ ዝኆን በረረ፡፡ ‹‹ነይ ወደ ወንዙ እንሂድ፤ ተከተይኝ፡፡ እዚያ አዞ ለእራት ምን እንደሚመገብ ታያለሽ›› በማለት ቁራ ለዝኆን ተናገረ፡፡

9

እናም ህፃኗ ዝሆን ቁራን እስከ ወንዙ ድረስ ተከተለችው፡፡

10

በሸንበቆዎቹ መካከል እየገሰገሰች ሄዳ ወንዙ ዳር ቆመች፡፡ ወደ ውሃውም ጎንበስ ብላ ተመለከተች፡፡ አዞው የት ነበር?

11

ከወንዙ ዳርቻ ያለ አንድ ድንጋይ ‹‹ጤና ይስጥልኝ›› አለ፡፡ ህፃኗ ዝኆንም ‹‹ጤና ይስጥልኝ›› አለች፡፡ ‹‹አዞ ለእራት ምን እንደሚበላ ንገረኝ?›› ብላ ጠየቀችው፡፡

12

ድንጋዩም ‹‹ዝቅ በይ፤ እኔ እነግርሻለሁ›› አላት፡፡ ድንጋዩ ‹‹ዝቅ፣ ዝቅ›› አለ፡፡ እናም ግልገል ዝኆን ዝቅ አለች፤ ዝቅ፡፡

13

ከዚያ በድንገት ‹‹ላፍ!›› የግልገል ዝሆን አፍንጫ በአዞ መንጋጋ ውስጥ ገባ። ቁራም ‹‹አዞ ለእራት ይበላሻል!›› በማለት በመጮህ እየበረረ ሸሸ።

14

ግልገል ዝኆን በጠንካራ እግሮቿ ተቀምጣ ጎተተች። ጎተት፣ ጎትት፡፡ አዞ ግን አፍንጫዋን አልለቀቃትም፡፡

15

የግልገል ዝኆን አፍንጫ ተለጠጠ፣ ተለጠጠ፣ ተለጠጠ፡፡ ከዚያ ‹‹እንዘጭ!›› በጀርባዋ ወደቀች፡፡

16

አዞው ተመልሶ ወደ ውሃው ውስጥ ገባ፡፡ እራት በማጣቱ ተናደደ።

17

ግልገሏ ዝኆን አፍንጫዋን ተመለከተች። በጣም ረዝሞ ነበር። እሷ መጨረሻውን ማየት አልቻለችም!

18

አፍንጫዋ በጣም ረዥም ስለሆነላት ከፍ ካሉ የዛፍ ቅርንጫፎች ፍሬ መሰብሰብ ትችላለች፡፡

19

አፍንጫዋ በጣም ረዥም ስለሆነላት ጀርባዋን ውኃ እየረጨች መታጠብ ትችላለች፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ሁሉም ዝኆኖች ረዥም እና ጠቃሚ ኩምቢዎች ኖሯቸው፡፡

20
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ጉጉ ግልገል ዝኆን
Author - Judith Baker, Lorato Trok
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Wiehan de Jager
Language - Amharic
Level - First sentences