አንዲት እናት ልጇን ታቅፋ ፍራፍሬ ለመልቀም ወደ ጫካ ትገባለች፡፡
በጫካ ውስጥም ስትጓዝ የበሰሉና የመሚያጔጉ ፍሬዎች የያዘ ዛፍ አገኘች፡፡
በመንገድ ላይ እንቅልፍ የወሰደውን ልጇንም ዛፍ ስር መሬት ላይ ታስተኛና ፍሬ ለማውረድ ከዛፍ ላይ ትወጣች፡፡
ከሌላ አካባቢ የመጣ አንድ ሽፍታ በአካባቢው ሲያልፍ ህፃኑን ይመለከተዋል፡፡ በጣምም ይደነቅና "እናቱ እዚህ ጥላው እንዴት ትሄዳለች?" በማለት ራሱን ይጠይቃል፡፡
ሽፍታው ዝቅ ብሎ፣ በጉልበቱ ተንበርክኮ ልጁን ሲመለከት አንገቱ ላይ ያነገተው ሠንሠለት ድምፅ ስለፈጠረ ድምፁ ህፃኑን ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡
ህፃኑም ሲነቃ አንገቱ ላይ ባለው ሰንሰለት መጫወት ጀመረ፡፡ ህፃኑም በጨዋታው በጣም ተደስቶ በሳቅ ይፍለቀለቅ ጀመር፡፡
እናቱም የልጇን ሳቅ ስትሰማ በምን ሊስቅ እንደቻለ ለማወቅ ቁልቁል በዛፉ ቅርንጫፎች መካከል ስትመለከት አንድ ሰው ከልጇ አጠገብ መኖሩን ተመለከተች፡፡
በዚህ ጊዜ እናት በጣም ደነገጠች፡፡ ከድንጋጤዋ ብዛትም በእጇ ይዛው የነበረው ፍራፍሬ የሞላ ከረጢት ከእጇ አምልጦ ወደቀ፡፡
በዚህ ጊዜ ሽፍታው ሰውዬም ወደ ዛፉ ቀና ብሎ ሲመለከት እናትየው በፍርሀት ስትንቀጠቀጥ አያት፡፡ ከዚያም "እባክሽ አትፍሪ፤ እኔ ከልጅሽ ጋር እየተጫወትኩ ነው እንጂ ምንም ጉዳት አላደረስኩበትም" በማለት እንድትረጋጋ ጠየቃት፡፡
እናትዮዋም ቀስ ብላ ከዛፉ ወረደች፡፡
ሽፍታውም አንገቱ ላይ ካደረገው የሰንሰለት ጌጥ ውስጥ አንዱን ሰንሰለት በማውጣት "ይኸውልህ፣ አንተ ቆንጆ ልጅ ይህ ጌጥ መጫወቻ ይሁንህ" በማለት ለህፃኑ ስጦታ ሠጠው፡፡
ሽፍታው ቀጠል አድርጎም “ልጅሽን ይዘሽ ወደ ቤትሽ መሄድ ትችያለሽ፡፡ ለባለቤትሽ ደግሞ ይሄ አካባቢ አደገኛ ሽፍታዎች የበዙበት ቦታ ስለሆነ ሌላ ሠላም ያለበት መኖሪያ አካባቢ እንዲወስድሽና በዚያ እንድትኖሩ ንገሪው” በማለት ተሰናብቷቸው ሄደ፡፡