አማትዮዋ
Abiyot Legesse
Jesse Breytenbach

አንድ ወጣት ከእናቱ ጋር ይኖር ነበር፡፡ ምግቡን የምታዘጋጀውም ሆነች ልብሱን የምታጥብለት እናትዮዋ ነበረች፡፡ ወጣቱ ሚስት አገባ፡፡ ሚስቱም ወደ ቤታቸው መጥታ መኖር ጀመረች፡፡ ለጊዜው ነገሮች ሁሉ በነበሩበት ቀጠሉ፡፡ ቆይቶ ግን ሁለቱ ሴቶች እርስበርሳቸው ይጣሉ ጀመር፡፡

1

አንድ ቀን ባልየው ከስራ አምሽቶ መጣ፡፡ ''እርቦኛል፤ የታል ራቴ?'' ሲል ጠየቀ፡፡ ሚስቱ ግን ምላሽ አልሰጠችውም፡፡ ''ችግሩ ምንድነው?'' በማለትም ደግሞ ጥያቄ አነሳ፡፡ በዚህን ጊዜ ሚስትዮዋ ማልቀስ ጀመረች፡፡ ''እናትህ አትወደኝም፡፡ ሁልጊዜ በክፉ ዓይን ታየኛለች፡፡ ከአሁን በኋላ ከእሷ ጋር አልኖርም'' አለችው፡፡

2

ሰውዬው ቆንጆዋን ሚስቱን አያት፡፡ ይወዳታል፡፡ ''በፈጠረሽ ተፋቅራችሁ ኑሩልኝ፡፡ ይህች ሴትዮ ከኛ ጋር ዘላለም አትኖርም፡፡ አሁን በቃ ርሽው፡፡ ራቴን ብቻ አምጪልኝ፡፡''

3

ሚስቱም ''ራት የለም! ይች አሮጊት እያለች እኔ ምግብ አልሰራም፡፡ ሁሌ ትሰድበኛለች'' አለች፡፡ ''እሺ ምን ይብጀኝ'' ሲል ሰውዬው ጠየቃት፡፡ ''እናቴ ነች፡፡ የምንኖርበትም ቤት የሷነው፡፡ አላባርራት'' በማለት ተናገረ፡፡ ''ወይ እኔን ወይ እሷን ምረጥ፡፡ ሁለታችን በአንድነት አንኖርም'' አለችው ሚስቱ፡፡

4

በዚያን ምሽት ሰውዬው ምግብ ሳይበላ ወደ መኝታው ሄደ፡፡ መተኛት ግን አቃተው፡፡ ''እንዲያው ምን ይሻለኛል'' ሲል አሰበ፡፡ ''እናቴንና ሚስቴን እንዴት ላበላልጣቸው? እናቴ እድሜዬን ሙሉ ፍቅሯን ለግሳኛለች፡፡ ሚስቴም ቆንጆ ወጣት ነች፡፡ ካለ እሷ መኖር አልችልም'' ሲል አሰበ፡፡

5

በማግስቱ ጠዋት ሚስቱ ''እህ፣ ባለቤቴ? የሚሆንህን መረጥክ?'' ብላ ስትጠይቀው፤ ''ሁለታችሁንም እኩል እወዳችኋለሁ'' በማለት መለሰላት፡፡ ''ሁለታችንንም እኩል መውደድ አትችልም'' አለችው ሚስቱ፡፡ ''እናትህን ግደላትና ለረጅም ዘመን በደስታ መኖር እንችላለን'' አለችው፡፡

6

ሰውየውም ወደ ስራ ቦታው ሄደ፡፡ ቀኑን ሙሉም ስለእናቱና ስለሚስቱ ሲያስብ ዋለ፡፡  ''ሚስቴ ያለችው ትክክል ነው'' ሲል አሰበ መጨረሻ ላይ፡፡ ''እናቴ አርጅታለች፡፡ ወደ ገደሉ ወስጄ እገፈትራታለሁ፡፡ ከዚያም ሚስቴና እኔ በደስታ መኖር እንችላለን'' በማለት አሰበ፡፡

7

ከማሳው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሚስቱ ''አሁንስ መረጥክ?'' በማለት ጠየቀችው፡፡ ''አዎ፣ አንቺን መርጫለሁ፡፡ እናቴን ነገ ገደል እጨምራታለሁ፡፡ አሁን ግን ስለራበኝ ራቴን አምጪልኝ'' ''እሺ''አለች ሚስትዬዋ፡፡ ''የምትወደውን ምግብ ሁሉ ሰርቼልሃለሁ፡፡ እናትህን ስትገድላት ደግሞ በየቀኑ ሁሉንም ዓይነት ምግብ እሰራልሃለሁ፡፡''

8

በማግስቱም ሰውዬው ''እማማ፣ እኔና አንቺ ወደ ተራራው እንሂድ፤ በጣም ዘና ትያለሽ'' አላት፡፡ እናትዬዋም ገረማት፡፡ ''አሁን አርጅቻለሁ፤ እዚያ ተራራ ድረስ እንዴት አድርጌ መውጣት እችላለሁ ብለህ ነው?'' ትለዋለች፡፡ ''ችግር የለም እኔ እሸከምሻለሁ'' አለ ልጇ፡፡ አንስቶም ሽክም አላት፡፡ በመጀመሪያ እናትዬዋ በደስታ ስታወራ ነበር፡፡ ልጇ ግን ምንም አላናገራትም፡፡ ወዲያውኑም እናትዬዋ መናገሯን አቆመች፡፡

9

መንገዳቸውን ግን ቀጠሉ፡፡ በኋላም እናትና ልጅ ከተራራው ጫፍ ላይ ደረሱ፡፡ ''ሁሉም ነገር ገብቶኛል ልጄ ሆይ! አንተ ግን እንዳትወድቅብኝ አደራህን፡፡ እኔን ስትወረውር የዚያን ዛፍ ቅርንጫፍ ጥብቅ አድርገህ ያዝ፡፡ ከያዝክ አትወድቅም'' አለችው፡፡ ልጅየውም በጣም ተገረመና ''እማማ'' አላት፡፡ ''ሁሉንም ነገር እያወቅሽውም ትወጅኛለሽ!'' አላት፡፡ ''እናት ብቻ እኮ ነች ፍቅርን የምታውቀው'' በማለት በሐዘኔታ ፈገግ አለች፡፡

10

ሰውዬው እናቱን መሬት ላይ አሳርፎ ከጎኗ ተቀመጠ፡፡ ራሱን በእጆቹ ይዞ ''ሚስቴ ይህን ያህል ትወደኝ ይሆን?'' በማለት አሰበ፡፡ ከዚያም ''ሚስቴ ተንኮለኛ ሴት ነች፡፡ ከዚህ በፊት ወድጃት ነበር፡፡ አሁን ግን ጠላኋት፡፡ እናቴን እጦራለሁ፡፡ ሚስቴን ግን አባርራለሁ'' ሲል ወሰነ፡፡

11

ሰውዬው እናቱን ተሸክሞ መልሶ ወደቤቱ ይዟት ሄደ፡፡ እናቱን ወደ ቤት ከወሰደ በኋላም ያችን ሚስቱን አባረራት፡፡ ከእናቱም ጋር ለረጅም ጊዜያት በደስታ ኖሩ፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
አማትዮዋ
Author - Abiyot Legesse, Elizabeth Laird
Translation - መዘምር ግርማ
Illustration - Jesse Breytenbach
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs