አንሱት
Fanie Viljoen
Stephen Wallace

ትምህርት ቤት የሰዓት ደወል ሲደወል ዞንኬ "ኢይፒ (Yippee)!" ብሎ ጮኸ። በመጨረሻ ወደ ቤቱ ሊሄድ ነው። ዛሬ ከሰዓት ከሌሎቹ ልጆች ጋር እግር ኳስ መጫወት ይፈልጋል።

"ሃይ! ተጠንቀቅ እንጂ፣" የሚል ድምፅ ድንገት ከፊቱ ተሰማ። ዞንኬ ቤካ ከፊቱ መቆሙን አላስተዋለም ነበር። ቤካ በቁጣ አጉረመረመበት።

1

"ይቅርታ፣" ዞንኬ በፍጥነት መለሰ። ቤካን አልፎት ለመሄድ ሞከረ። ነገር ግን ቤካ ድንገት ገፋው። ዞንኬ ተዝረከረከ። ቤካም እየሳቀ "ለመውደቅ እንዲህ የቀለለህ እግርህ በጣም ትልቅ ስለሆነ ነው?" እያለ አፌዘበት።

ዞንኬ ተበሳጭቶ ራሱን አቀና። ታንዲ የምትባል አንዲት ሴት ልጅ ረዳችው። ዞንኬም "አመሰግናለሁ" አላት። ታንዲም "ምንም አይደለም፤ ሁሉንም አይቻለሁ። ቤካ በእርግጥም ጉልበተኛ ነው" አለችው።

2

ዞንኬ ወደ ቤቱ እየሮጠ ሄደ። አየሩ በጣም ሞቃታማ ነበር፤ ግን እድለኛ ሆኖ ቤቱ ብዙም ሩቅ አልነበረም።

ድንገት፣ በመንገዱ ላይ አንድ ነገር ተመለከተ። ቆመ። ምንድን ነው? መጠኑ ልክ እንደ እጁ መዳፍ የሚያክል ትልቅ ነው። ቀለሙ ቡናማ ሲሆን፣ የተሰራውም ከቆዳ ነው።

3

የኪስ ቦርሳ ነው! ዞንኬ በእድለኝነቱ ማመን አቃተው።

በፍጥነት የቦርሳውን ውስጠኛ ክፍል በዓይኑ አማተረ። ዋው! ውስጥ መቶ ብር (ገንዘብ) አለበት!

4

የዞንኬ ልብ በፍጥነት መምታት ጀመረ። ከዚያም ቦርሳውን በኪሱ ውስጥ ከተተው። ማንም ሰው አይቶት እንደሆነ ለማረጋገጥ በፍጥነት ዙሪያውን አማተረ።

አዎ! አንድ ሰው እየመጣ ነው። ቤካ ነው! ከዞንኬ ጥቂት እርምጃዎች ብቻ ርቆ በስተጀርባው ይከተለዋል።

5

ዞንኬ ጉዞውን አፋጠነ። ቤካ እንዳላየው ተስፋ አደረገ። ደግሞ ደጋግሞ ወደ ኋላው መመልከት አልፈለገም።

የኪስ ቦርሳው በኪሱ ውስጥ በሰላም ተቀምጧል። ቤት ሲደርስ አውጥቶ ምን ያህል ገንዘብ እንዳለው ለማየት ወሰነ።

6

ቤት እንደደረሰ ዞንኬ የትምህርት ቤት ቦርሳውን አስቀመጠ። ከዚያም በቤቱ አጠገብ ወዳለው ጥላማ ዛፍ ስር አመራ። በጥንቃቄ ቦርሳውን ከኪሱ አወጣው። ልቡ በፍጥነት ይመታል!

ገንዘቡን መቁጠር ጀመረ። ሃምሳ... መቶ... መቶ ሃምሳ... ሁለት መቶ ራንድ! አሁን እጅግ ባለጸጋ የሆነ መሰለው። ነገር ግን፣ ድንገት ያ የሚያውቀው ድምፅ ተሰማ። "ምን እየደበቅክ ነው?" ቤካ ነው!

7

ዞንኬ የኪስ ቦርሳውን ከጀርባው ደበቀ። ቤካ ግን "ረፍዶብሃል! የሆነ ነገር ስታነሳ አይቼሃለሁ፣" አለው። "ለዛ እኮ ነው ምን እንደሆነ ለማየት የተከተልኩህ።"

ቤካ የዞንኬን እጅ በኃይል ጎተተው። ቦርሳውን ሲያይ ዓይኖቹ በገረሜታ ፈጠጡ። ቀምቶም ወሰደው። "ዋው! ይሄ በጣም ቆንጆ ነው! ልታስቀምጠው ነው እንዴ?" ሲል ቤካ ጠየቀው።

8

"ገና አላወቅኩም፣" ዞንኬ እየተንተባተበ መለሰ። ቤካም ገንዘቡን መቁጠር ጀመረ። "ያንን አባባል ታውቀዋለህ፡ 'ያገኘ የኛው'።" ቤካ በፉጨት አጀበው። "በእርግጠኝነት ለራስህ ማድረግ አለብህ። እኔ ብሆን ኖሮ ለራሴ አደርገው ነበር።"

"ግን እኮ የሆነ ሰው ነው የጠፋበት፣" አለ ዞንኬ። ቤካ ግን ሳቀ። "ቢሆንስ? እነሱ ጥንቃቄ ስላልነበራቸው ነው። ስለዚህ አሁን ገንዘቡ የአንተ ነው።"

9

"ስለ ጉዳዩ ማሰብ ይኖርብኛል፣" አለ ዞንኬ። ቤካ ግን "ስለ እሱ ማሰብ አያስፈልግህም፣" አለው። "ምን ማድረግ እንዳለብህ ልንገርህ፤ ገንዘቡን ለራስህ አድርገው። አዲስ ጫማ ወይም የእግር ኳስ ግዢበት።"

"አይሆንም!" የሚል የሴት ልጅ ድምፅ ተሰማ። ከትምህርት ቤት የምታውቀው ታንዲ ነበረች። "ዞንኬ፣ ገንዘቡ የአንተ አይደለም። ለራስህ ለማድረግ ምንም መብት የለህም።"

"ታንዲ፣ አንቺ ምን አገባሽ?" ሲል ቤካ ጠየቃት። ፊቱን እያጠማዘዘም "አንቺ ዝም ብለሽ አዋቂ ለመምሰል ትሞክሪያለሽ። ዞንኬ ገንዘቡን መመለስ የለበትም" አላት።

10

ዞንኬ የሁለቱንም ክርክር አዳመጠ። ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው። ገንዘቡን ለራሱ ቢያደርገው ደስ ይለው ነበር። ነገር ግን የታንዲ ሃሳብ ትክክል ሊሆን ይችላል። የአንተ ያልሆነን ነገር መውሰድ አትችልም፤ ምንም እንኳ በመንገድ ላይ ያገኘኸው ቢሆንም።

ቤካ ድንገት ከፊቱ ገጭ ብሎ ቆመ። እጆቹን አጣጥፎም "እሺ ዞንኬ፣ ምን ልታደርግ ነው? ገንዘቡን ለራስህ ታደርገዋለህ? ወይስ ባለቤቱን ለመፈለግ ትሞክራለህ?" ሲል ጠየቀው።

ዞንኬ ደጋግሞ አሰበ። በመጨረሻም በታላቅ ድምፅ "እመልሰዋለሁ!" አለ።

11

ታንዲ ፈገግ አለች። "ትክክለኛው ውሳኔ ይሄ ነው። ውጤቱን ደግሞ ታየዋለህ" አለችው።

ቤካ ራሱን በመነቀነቅ ቦርሳውን ለዞንኬ መለሰለት። "ፈሪ ነህ!" ብሎት ጥሏቸው ሄደ።

ታንዲ በለስላሳ ድምፅ "ፈሪ አይደለህም፣" አለችው። "ገንዘቡን ለራስህ ብታደርገው ኖሮ አንተም እንደ ቤካ አስቀያሚ (መጥፎ) ትሆን ነበር።"

ዞንኬ ፈገግ አለ። ትክክለኛውን ውሳኔ እንድትወስን ስለረዳችው ደስ አለው። "ለመሆኑ የገንዘቡ ባለቤት ማን እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?" ሲል ጠየቀ።

12

ታንዲ የኪስ ቦርሳውን ውስጠኛ ክፍል አየች። አንድ የባንክ ካርድም አወጣች። በካርዱ ላይ ጉጉ ዱቤ የሚል ስም ተጽፏል። ስሙ ለዞንኬ የሚታወቅ ይመስላል።

ታንዲ ሌላ ነገር ደግሞ ከቦርሳው ውስጥ አወጣች። የጉጉ እና የልጆቿ ትንሽ ፎቶግራፍ ነበር።

አሁን ዞንኬ አወቃት። "እሷ እኮ እዚህ አቅራቢያ ነው የምትኖረው! ነይ ተከተይኝ። ቦርሳዋን ልንመልስላት እንሄዳለን" አላት።

13

ዞንኬና ታንዲ በጠጠር መንገዱ ላይ አብረው ሮጡ። የአክስት ጉጉ ቤት በር ተከፍቶ ነበር።

በሩን አንኳኩ። በቅጽበት አንድ ሰው ወደ በሩ መጣ። አክስት ጉጉ ነበረች። ምስኪን፣ እያለቀሰች ትመስላለች።

14

ዞንኬ አክስት ጉጉ በማልቀሷ በጣም አዘነ። ነገር ግን ወዲያውኑ የኪስ ቦርሳውን ከኪሱ አወጣ። የአክስት ጉጉ ያዘነ ፊት ወዲያውኑ ወደ ደስታ ተለወጠ፤ በሳቅም ተሞላች።

"ቦርሳዬ!" ብላ ጮኸች። "ማመን አቃተኝ!" በቦርሳው ውስጥ ያለውን ገንዘብ አረጋገጠች። "ገንዘቡም ሁሉ እዚህ አለ። በጣም ደስ ብሎኛል። ምግብ ልገዛ ስወጣ ነበር ቦርሳዬን የጣላሁት። በዚህ ሳምንት የምንበላው አጥተን በረሃብ የምናድር መስሎኝ ነበር።"

ሁለቱንም፣ ዞንኬንና ታንዲን ግንባራቸውን ሳመቻቸው። ከዚያም በታላቅ ደስታ በቤቷ ውስጥ ጨፈረች።

15

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ዞንኬ እና ታንዲ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ዞንኬ ክብር የሚሰጠውንና ትክክለኛውን ነገር በማድረጉ እጅግ ተደስቷል።

ታንዲ ትክክል ነበረች። ቦርሳውን ለራሱ ቢያስቀረው ኖሮ፣ እሱም ልክ እንደ ቤካ አስቀያሚ (መጥፎ ሰው) ይሆን ነበር። ዛሬ ግን ዞንኬ በልቡ ውስጥ እውነተኛ ጀግና እንደሆነ ተሰማው!

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
አንሱት
Author - Fanie Viljoen
Translation - Tesfamichael Hailu,Natnael Argaw
Illustration - Stephen Wallace
Language - Amharic
Level - Read aloud