ዓሣ እና ስጦታ
Liesl Jobson
Jesse Breytenbach

በአንዲት ልዩ አርብ ዕለት አንዲት የብርሃን ፍንጣቂ ሰማዩን ከማብራቷ በፊት የዩሱፍ አባት ልብሶቻቸውን ለባበሱ፡፡ ከባድ የዝናብ ልብሳቸውን ለበሱ፤ እስከ ጆሯቸው ድረስ የሚሸፍነውን አረንጓዴ የሱፍ ኮፍያቸውን አደረጉ፡፡ ለልጃቸውም በእጃቸው የስንብት ምልክት አሳዩት፡፡ አባትዬው ለዩሱፍ ‹‹ዛሬ ዓሣ የማጠምድበት ቀን ስለሆነ ስጦታ አመጣልሃለሁ›› ሲሉት ዓይኖቹ በብርሃን ተሞሉ፡፡

1

ዓሣ እና ስጦታ? ኦ፣ ምን ሊሆን ይችላል? አባትዬው ወደ ሙዘንበርግ የወንዝ ዳርቻ በብስክሌት ወረዱ፡፡ የብስክሌቷም ሰንሰለት እስከ ጀልባ ቀዛፊዎቹ ስፍራ እስኪደርሱ ድረስ ሲጥጥ ሲጥጥ ሲል ቆየ፡፡ ባለ ረጃጅም ክንፍ ወፎች ሰማዩን ከበውታል፡፡ ‹‹ምን? ምን? ምን?›› በማለትም ይጮሁ ጀመር፡፡ ‹‹ለዩሱፍ ይዘህለት የምትሄደው ምንድነው?›› እያለ አባባ ደወሉን ደወለ፡፡ ‹‹ጠብቁና ምን እንደሆነ እዩ!››

2

ዓሣ አጥማጆቹ ፀሐይዋ ስትወጣ አዩዋት፡፡ የዓሣ ማጥመጃ መረቦቻቸውን አወጡ፡፡ መቅዘፊያዎቻውን አነሱ፡፡ ነፋሱንም አዳመጡ፡፡ ጀልባዎቻቸውንም ወደ ዉኃው ጎተቱ፡፡ ኡፓ ሳሊ የተባሉት የዩሱፍ አያት፣ ዓሣ አጥማጅ ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው በፊትም አባታቸው ኡፓግሮትጄ ሪድዋን ባህሩን በሚገባ ያውቁት ነበር፡፡

3

ጀልባዋ ነፋሱን ተከትላ ትቀዝፍ ጀመር፡፡ የአባባ ክንዶች አግድም መቅዘፊያውን ይዘዋል፡፡ እግሮቻቸውም ወደ ጎን ተዘርግተዋል፡፡ አንገታቸው ቀጥ ብሏል፡፡ ጀርባቸው ይወዛወዛል፡፡ አባባ እየሰሩ ይዘፍናሉ፡፡ ‹‹ውደቅ አንሣ፤ ፈልግ ዓሣ፡፡ ሳበው ዛቀው፤ እንዳትለቀው፡፡››

4

ዩሱፍ ቀኑን ሙሉ ሰማይ ሰማዩን ሲያይ ዋለ፡፡ ብሩህ፣ ንፁህና ነፋስ አልባ ሰማይ ነው፡፡ ዓሣና ስጦታ! አባባ ከባህሩ ምን ይሆን የሚያመጣልኝ? አንዳንዴ ቆንጆ ዛጎል ያመጣልኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ማዕበል ያንሳፈው አረንጓዴ የጠርሙስ ጌጥ ያመጣል፡፡

5

አንዳንዴ የዩሱፍ አባት ተረት ያመጣሉ፡፡ አሸዋው ላይ ማዕበል ያመጣቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የወንዝ ዔሊዎች ያገኙ ጊዜ እንደሆነው ሁሉ፡፡ ‹‹ምን? ምን? ምን?›› በማለት ባለ ረጃጅም ክንፎቹ ወፎች ጮሁ፡፡ ‹‹ዔሊዎቹን እንዴት ታግዛቸዋህ?›› አባባ ‹‹እነዚያን ዔሊዎች አድነናቸዋል አልኩህ፡፡ መልሰን ወደ ውቅያኖሱ አስገባናቸው፡፡ አንድም ሳይቀር፡፡››

6

ሁልጊዜ አባባ ዘፈን ያመጣል፡፡ መቅዘፊያዎቹን ይዞ ሲቀዝፍ ይዘፍናል፡፡ መረቦቹን ሲስብ ይዘፍናል፡፡ ገመዶቹን ሲጠቀልል ይዘፍነዋል፡፡ ወደ ቤት በብስክሌት ሲመጣ ይዘፍናል፡፡ ‹‹ውደቅ አንሣ፤ ፈልግ ዓሣ፡፡ ሳበው ዛቀው፤ እንዳትለቀው፡፡››

7

ኡማ ሳፊያ ለራት ቆንጆ ወፍራም ባለቢጫ ጭራ ዓሣ መብላት ትፈልጋለች፡፡ ‹‹ግን ትንሽዬም ዓሣ እንኳን ካጠመዱ ደስተኞች እንሆናለን፡፡ ዛሬ የዓሣ ጭራ የሚበላበት አርብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወንዙ ውስጥ ብዙም ዓሣ የለም፤ አልቋል፡፡›› አለች ኡማ ራሷን እየነቀነቀች፡፡ ዩሱፍ የኡማን እጅ ያዘ፡፡ መታጠቢያ ቤቱ ጋ ያለውን መንገድ አቋረጡ፡፡ ‹‹ምን? ምን? ምን?›› በማለት ባለ ረጃጅም ክንፎቹ ወፎች በአንጸባራቂዎቹ ጣራዎች ላይ ሆነው ጮሁ፡፡ ‹‹ለራት የምትበሉት ምንድነው?››

8

ባለፈው ዓመት ዓሣ አጥማጆቹ ከቀዛፊዎቹ ጋር ተጣልተው ነበር፡፡ እጃቸውን እየሰነዘሩ ሲጯጯሁ ‹‹ምን? ምን? ምን?›› በማለት ባለ ረጃጅም ክንፎቹ ወፎች ጮሁባቸው፡፡ የዩሱፍ አባትም ‹‹ለሁላችሁም የሚበቃ ወንዝ አለ እኮ›› አሉ ፡፡ የኡፓ ሳሊን ዓሣ የማስገሪያ ፈቃድ አሳዩዋቸው፡፡ ‹‹ሞገዶ ለሁሉም፡፡ ዉኃ በነጻ›› ይላል፡፡

9

ኡማ ሳፊያ በመነጽሯ ታያለች፤ እጆቿም በጉጉት መነጽሩን ይዘዋል፡፡ የዓሣነባሪን መምጣት የሚያስጠነቅቀው ድምጽ ጮኸ፡፡ ዋናተኞች ወደ አሸዋው ተመልሰው ፎጣዎቻቸውን ያዙ፡፡ ቀዛፊዎች መቅዘፊያቸውን በክርኖቻቸው ስር ይዘው ወደ ዳርቻ ወጡ፡፡ በዝናብ እርጥብ ልብሶቻቸውን አወለቁ፡፡ ‹‹ምን? ምን? ምን?›› በማለት ባለ ረጃጅም ክንፎቹ ወፎች ጮሁ፡፡ ‹‹የዩሱፍ አባት ከባህሩ ምን ይዞ ይሄዳል?››

10

የዩሱፍ አባት፣ አጎቶችና የአጎቶች ልጆች እያቃሰቱ ይስባሉ፡፡ ትንሽ ዓሣነባሪ ተይዟል፡፡ ሞገዱ ሳያግደው ይታገላል፡፡ የዩሱፍ አባት ለዓሣነባሪው እየዘፈኑ መረቦቹን ይፈታታሉ፡፡ ‹‹ውደቅ አንሣ፤ ፈልግ ዓሣ፡፡ ሳበው ዛቀው፤ እንዳትለቀው፡፡›› በመጨረሻም ዓሣነባሪው ምንም እንዳልያዘው አውቆ ወደ ሞገዱ ገባ፡፡ መረቡም ላይ አንድ ትልቅ ባለቢጫ ጭራ ዓሣ ብቻ ቀረ፡፡ ኡማ ሳፊያ ትደሰታለች፡፡

11

ሰዎቹ ጀልባዋን ስበው ገመዶቹን ጠቀለሉ፡፡ የአባባን ጣት አንድ ነጭ ጠጣር ሦስት ጎን ያዛቸው፡፡ ‹‹ምን? ምን? ምን?›› በማለት ባለ ረጃጅም ክንፎቹ ወፎች ጮሁ፡፡ ‹‹ለዩሱፍ ምን አመጣህለት?›› ፀሐይዋ ስትጠልቅ አባባ ለባለ ረጃጅም ክንፎቹ ወፎች መለሱላቸው፡፡ ‹‹ለልጄ የዓሣነባሪ ጥርስ፡፡›› እቤት ሲደርሱ ዩሱፍ ስጦታውን ወደ ኮከቦቹ ከፍ አድርጎ ያዘ፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ዓሣ እና ስጦታ
Author - Liesl Jobson
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Jesse Breytenbach
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs