

በዱሮ ጊዜ አንድ ዋያን የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ዋያን የሚኖረው በኢንዶኔዢያ በባሕር ዳር በምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ነበር፡፡ መንደሯ የምትገኘው በአንድ ትልቅ በእሳተገሞራ ፍንዳታ በተፈጠረ ተራራ ጥግ ነበር፡፡ በእሳተገሞራው ምክንያትም ሁሉም የባሕሩ ዳርቻዎች በጥቁር አሸዋ የተሸፈኑ ነበሩ፡፡ መንደርተኞቹ ሩዝ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ኮኮናት፣ ፓፓያ፣ የእባብ ፍሬና የድራጎን ፍሬ የተባሉትን ያመርቱ ነበር፡፡ ስለሆነም አንድም የሚራብ ሰው አልነበረም፡፡ ባሕሩ ለመንደርተኞቹ በጣም አስፈላጊ ነበር፡፡ ከጥንት ጀምሮ ዘር ማንዘሮቻቸው ሁሉ የኖሩበት ነው፡፡ መንደርተኞቹ ሰው ሲሞት ወደ ባሕሩ ይመለሳል ብለው ያምኑ ነበር፡፡
የዋያን አባትና አያት ዓሣ አጥማጆች ነበሩ፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ በመንደሩ የነበሩ ሰዎች ዓሣ አጥማጆች ነበሩ፡፡ ከጥንት ጀምሮም ተመሳሳይ ነበር፡፡ አንድ ሰው ዓሣ አጥማጅ ለመሆን ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ዋያን ሲያድግም ዓሣ አጥማጅ ይሆናል፡፡ በየቀኑ ማለዳ ፀሐይ ስትወጣ ወንዶቹ ጁኩንግ የተባለችውን ጀልባ ይዘው ወደ ባሕሩ ዓሣ ለማጥመድ ይሄዳሉ፡፡ ማታ ፀሐይ ስትገባ ደግሞ ጀልባዎቻቸውን በዓሣ ሞልተው ይመለሳሉ፡፡ በባሕሩ ትላልቅ፣ ትናንሽ፣ ግራጫና ባለቀለም ዓሣዎች ነበሩ፡፡
አንድ ቀን የዋያን አያት ታመው ሞቱ፡፡ ሁሉም ሰው አዘነ፡፡ ለስንብት ትልቅ ዝግጅት አዘጋጅተው ሬሳቸውን አቃጥለው አመዱን የዘር ማንዘሮቻቸው ቤት ወደ ነው ተብሎ ወደሚታመነው ወደ ባሕሩ ጨመሩት፡፡
ጊዜው እየሄደ ሲመጣ ዋያንም አደገ፡፡ ዋያን ዓሣ አጥማጅ ሲሆን፤ አባቱም እያረጁ መጡ፡፡ አንድ ቀን ዋያን የቤተሰቡ መሪ ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን መማር ያለበት ብዙ ነገር አለ፡፡ ነገሮች እየተቀያየሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በባሕሩ ውስጥ ያሉት ዓሣዎች ቁጥር ስለተመናመነ ዓሣ አጥማጆች በባሕሩ ላይ ዓሣ ፍለጋ ከበፊቱ ለበለጡ ቀናት ይቆያሉ፡፡ አንዳንድ ቀን ከእንጨት የተሰሩት ጀልባዎች ከጠዋት እስከ ማታ ባሕር ላይ በዓሣ ፍለጋ ቢውሉም ባዷቸውን ይመጣሉ፡፡
ያ ሁሉ ዓሣ የት ሄደ? ዓሣ ያጠመዱ ጊዜም የሚያገኟቸው ዓሣዎች ሁሉ ትናንሽና የማይጣፍጡ ናቸው፡፡ የባሕሩ ዳርቻዎችም ተቀይረዋል፡፡ በፊት ንጹህና ማራኪ እንዳልነበሩ አሁን በየቦታው ፕላስቲክ ይታያል - የፕላስቲክ ኩባያዎች፣ የውኃ ኮዳዎች፣ መጠጥ መሳቢያ ቀጫጭን ላስቲኮች፣ ቦርሳዎችና ነጠላ ጫማዎችም ሳይቀሩ!
ብዙ ቆሻሻ በመኖሩ ምክንየት ከታች ያለውን ጥቁር አሸዋ ማየት እንኳን አዳጋች ነበር! መንደርተኛው እንዴ ብቻ የተጠቀመባቸውን ነገሮች ይወረውራል፡፡ መሬት ላይ ቆሻሻ ከመጣላቸው በፊት ሁለቴ አያስቡም፡፡ በየቦታው ፕላስቲክ ማየት የተለመደ ሆነ፡፡ የሩዝ ማሳዎች ሳይቀሩ በፕላስቲክ ተሸፈኑ፡፡ መደርተኞቹ አንዳንዴ ፕላስቲክ ያቃጥላሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቆሻሻቸውን ወደ ደረቀው ወንዝ ይጥላሉ፡፡ ማዕበል ሲመጣ ወይ ዝናብ ሲዘንብ ቆሻሻውን አጥቦ ይዞት ስለሚሄድ ችግሩም አብሮ ይሄዳል፡፡ ሰዎች እንደዚያ ሳይሆን አይቀርም ያሰቡት …
የመንደሩ ሰዎች መታመም ጀመሩ፡፡ ምክንያቱን ግን ማንም አላወቀውም፡፡ ‹‹ዓሣ ለምን ጠፋ? ሰው ሁሉ ለምን ይታመማል? እነዚህን ሁሉ መጥፎ ነገሮች እንዴት እናስቁማቸው?›› በማለት መንደርተኞቹ ተጨነቁ፡፡
አንድ ቀን ዋያን ዓሣ ሲያጠምድ ወደ ባሕሩ ወደቀ፡፡ ሊሰምጥ ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ አንድ የባሕር ዔሊ አተረፈው፡፡ የዔሊው ስም ኮከብ ነበር፡፡ ‹‹ጀርባዬ ላይ ውጣ፡፡ ሃሳብክን በኔ ላይ ጣለው›› አለው፡፡
‹‹አመሰግናለሁ ዔሊ፡፡ ሕይወቴን ስላተረፍክልኝ ውለታህን በምን እከፍልህ ይሆን?›› አለ ዋያን፡፡ ‹‹እስኪ እንግዲህ፣ ልትረዳኝ ትችል ይሆናል፡፡ አያቴ 200 ዓመቱ ነው፡፡ ከማውቃቸው ዔሊዎች ሁሉ ብልሁ እሱ ነው፡፡ በጣም ታሞብን ምን እንደምናደርግ ጨንቆናል፡፡ ምናልባት ታግዘው ይሆናል›› ሲል ጠየቀ ኮከብ፡፡
ኮከብ ዋያንን ወደ ዔሊ ከተማ ወሰደው፡፡ እዚያም ዋያን በርካታ ታዳጊ ዔሊዎችን የሚያይ መስሎት ነበር፡፡ እንዳሰበው አላየም፡፡ በብዛት ያየው በየቦታው የተጣለ ፕላስቲክ ነው፡፡ ኮከብ ዋያንን ከአያቱ ጋር አስተዋወቀው፡፡ አያትየው በጣም በጣም ስለታመሙ መናገርም ሆነ መተንፈስ አዳግቷቸዋል፡፡ ዋያን በኮከብ አያት አፍንጫ ላይ የተሰካ እንግዳ ነገር አየ፡፡ እሱም ‹‹ቆይ! ይህን እንግዳ ነገር ለማውጣት ልሞክር፡፡ ግን ትንሽ ሊያማቸው ይችላል፡፡ እሺ?›› አለ፡፡
ያንን ነገርም ሳበ፤ ሳበ፤ ሳበ፡፡ የኮከብ አያት ስላመማቸው ጮሁ፡፡ በመጨረሻም አወጣላቸው፡፡ ምንድነው? አጥንት ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ መጠጥ እየሳቡ መጠጫ የፕላስቲክ ቱቦ ነበር! የፕላስቲክ መሳቢያ? በዔሊ አፍንጫ ውስጥ? እንዴት ሊገባ ቻለ?
‹‹ኦ! አመሰግናለሁ ዋያን! ሕይወቴን አተረፍከው! አሁን እንደ በፊቱ መተንፈስ እችላለሁ›› አሉ፡፡ ‹‹ጋሊህ እባላለሁ፡፡ የዔሊዎች ንጉሥ ነኝ›› አሉት፡፡ ዋያን ለንጉሡ ክብር አጎነበሰ፡፡
በግዛቴ ያሉትን የታመሙ ዔሊዎች ሁሉ ላሳይህ፡፡ እባክህ ተከተለኝ›› አሉት ንጉሥ ጋሊህ፡፡ ብዙ ሕመምተኛ ትልልቅና ትንንሽ ዔሊዎች ታመው ወደተኙበት የዔሊዎች ሆስፒታል ሄዱ፡፡ ‹‹ምን ሆነው ነው?›› ሲል ጠየቀ ዋያን፡፡ ‹‹አናውቅም›› አሉ ንጉሡ፡፡ ‹‹ዓሣ በልተው ነው የታመሙት፡፡ ዓሣ ግን ዘላለማችንን እንደበላን ነን፡፡ ማንም ታሞ አያውቅም ነበር፡፡››
ንጉሥ ጋሊህ አንዱን ከታመመ ዔሊ ውስጥ የወጣውን ዓሣ ለዋያን አሳዩት፡፡
‹‹ይህ ዓሣ አይደለም፡፡ ፌስታል ነው! ለምንድነው ፕላስቲክ ነገር የምትበሉት ንጉሥ ጋሊህ? ምግብ አይደለም!›› አላቸው ዋያን፡፡
ንጉሥ ጋሊህም እንዲህ ሲሉ አብራሩለት፡፡ ‹‹እኛ ዔሊዎች በደንብ አይታየንም፡፡ ፌስታሉ ዓሣ ይመስለናል፡፡›› ከዚያም ንጉሡ አንድ ውለታ እንዲውልላቸው ጠየቁት፡፡ ‹‹ልትረዳን ትችል ይሆን? ሰዎች ፌስታልና የመጠጥ መጠጫ የላስቲክ ቱቦ እንዳይጠቀሙ ትነግርልን ይሆን? እዚህ ያየኸውን ልትነግርልን ትችል ይሆን? እባክህ፡፡ እርዳታህን እንፈልጋለን፡፡ ያለዚያ መሞታችን ነው፡፡››
ዋያንም ለንጉሡ አጎንብሶ ዔሊዎችን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገባላቸው፡፡ ኮከብ አዝሎት ወደ መንደሩ ተመለሰ፡፡ በመልስ ጉዞውም በውኃው ላይ ብዙ ፌስታሎችን አየ፡፡ በእርግጥም ዓሣ ይመስሉ ነበር! ዋያን በድንገት መንደርተኞቹ በአካባቢያቸው ያለውን የፕላስቲክ ቆሻሻ ፈጽሞ ልብ እንዳላሉት ገባው፡፡ ሁኔታው መቀየር እንዳለበትም ተገነዘበ፡፡ መንደርተኞቹን ሰብስቦ በጉዞው ስላየው ነገር ሁሉ አብራራላቸው፡፡
በዚያኑ ምሽት የመንደሩ አለቃ የሚከተሉትን ሕጎች አወጣ፡፡
ፌስታሎች፣ ከፕላስቲክ የተሰሩ መጠጫዎች፣ ኮዳዎችና ኩባያዎችን መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ፕላስቲክን አታቃጥሉ፡፡
ፕላስቲክን መሬት ውስጥ አትቅበሩ፡፡ የባሕሩን ዳር፣ መንደሩንና የሩዝ ማሳውን አጽዱ፡፡ ከሚሰበሰበወው የፕላስቲክ ቆሻሻ ጠቃሚ ነገሮችን ስሩ፡፡ ከባሕሩ ዓሣ ሳይሆን ፕላስቲክ ሰብስቡ፡፡ ባሕሩ እስኪጸዳ ዓሣ አታጥምዱ፡፡
ሥራው ከባድ ነበር፤ ለተወሰነ ጊዜም ሰዎች አትክልት፣ ፍራፍሬና ሩዝ እንጂ ዓሣ አልበሉም፡፡ በመጨረሻም ከሦስት ዓመታት የማጽዳት ሥራ በኋላ በሩዝ ማሣውም ሆነ በባሕሩ ምንም የፕላስቲክ ቆሻሻ አልነበረም፡፡ ሰዎች ፕላስቲኩን ወንበርና ጠረጴዛ ወደመሳሰሉ ጠቃሚ ነገሮች ቀየሩት፡፡ አንዴ ተጠቅሞ የሚጣሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን መጠቀም አቆሙ፡፡ በፕላስቲክ የመጠጥ መጠጫዎች ምትክ መቃ መጠቀም ጀመሩ፡፡ በፌስታል ምትክ ደጋግሞ መጠቀም የሚቻለውን የጨርቅ ቦርሳ መጠቀም ጀመሩ፡፡ በፕላስቲክ ኩባያዎች ምትክ እንደገና መጠቀም የሚቻለውን እንደ ብርጭቆ ያለውን መጠቀም ቻሉ፡፡ የአያቶቻቸው የኑሮ ዘይቤ አባካኝ ከሆነው ከነሱ ዘመናዊ አኗኗር የተሻለ እንደሆነ ተማሩ፡፡
መንደርተኞቹ የተፈጥሮ አካል መሆናቸው ገባቸው፡፡ እንስሳትና መሬት ጤናማ ከሆኑ እነሱም ጤናማ ይሆናሉ፡፡ እንስሳትና መሬት ከታመሙ እነሱም ይታመማሉ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ በባሕሩ እንደገና በሺዎች የሚቆጠሩ ዓሣዎች ተራቡ - ትላልቆች፣ ትናንሾች፣ ግራጮች፣ ባለ ብዙ ቀለማት ዓሣዎች፡፡ መንደርተtኞቹ መታመም አቆሙ፡፡ ዓሣዎቹና ዔሊዎቹም ጤናማ ሆኑ፡፡ ሰዎቹ ተደሰቱ፡፡ መሬቷ ተደሰተች፡፡ ዘር ማንዘሮቻቸው ተደሰቱ፡፡ ውቅያኖሱም ተደሰተ፡፡ ተፈጸመ፡፡
ጥያቄዎች
1. ዋያን የሚኖረው የት ነው?
2. አሸዋው ምን ዓይነት ቀለም አለው?
3. እውነት ወይስ ውሸት? የዋያን አባትና አያት ዓሣ አጥማጆች ናቸው፡፡
4. ንጉሥ ጋሊህ ለምን ታመሙ?
5. ንጉሥ ጋሊህ ዋያንን ምን እንዲያደርግላቸው ጠየቁት?
6. መንደርተኞቹ ምን ዓይነት ሕግ አወጡ?
7. ዓሣ ማጥመድ ለምን ያህል ጊዜ አቆሙ?
8. ተረቱን ወደድከው/ወደድሽው? ለምን?
9. ንጉሥ ጋሊህንና ዔሊዎቹን እንዴት ልታግዛቸው/ልታግዣቸው ትችላለህ/ትችያለሽ?

