

ስሙ አቡላ የሚባል ትንሽ ልጅ በአንድ መንደር ውስጥ ይኖር ነበር፡፡
አቡላ ማንበብ ቀርቶ መጽሐፍ መግለጥ እንኳ አይወድም፡፡ ሰነፍ ተማሪ ነው፡፡ መጥፎ ባህሪ አምጥቷል፡፡
አቡላ ብስኩት ለመግዛት የእናቱን ገንዘብ ሰረቀ፡፡ እናቱ ገንዘባቸውን ቢደብቁት እንኳ ፈልጎ ያገኘዋል፤ ይወስድባቸዋል፡፡
አቡላ በሙሉ ብስኩቱን በልቶ ከጨረሰ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር ይጫወታል፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ አቡላ ወደ ትምህርት ቤት መግባቱን አቆመ፡፡ ቀኑን ሙሉ እውጭ እየተጫወተ ይቆያል፡፡ ሲመሽ ብቻ ወደ ቤት ይመለሳል፡፡
የአቡላ እናት ድርጊቱን ተገነዘቡ እና ስለ ድርጊቱ ተጨነቁ፡፡
"ልጃችን ጥሩ እየሠራ አይደለም፡፡ ወደ ትምህርት ቤት የሄደ አይመስለኝም፡፡ ከእኔም ገንዘብ ሰርቋል" አሉ የአቡላ እናት፡፡
አባቱም የአቡላን መጥፎ ባህሪ ለመለወጥ የትኛው ዘዴ የተሻለ እንደነ ማሰላሰል ጀመሩ፡፡
አባቱ "ለሚቀጥለው፣ ገንዘቡን በመጽሐፍ ገጾች መካከል ደብቂበት፡፡ እሱ ፈጽሞ መጽሐፍ አይገልጥም፡፡ ስለዚህ ገንዘቡ የሚጠበቅልሽ እዚያ ሲሆን ነው" አሉ ለሚስታቸው፡፡
በሚቀጥለው ቀን፣ አቡላ የእናቱን ገንዘብ ይፈልግ ነበር፡፡ በሁሉም ቦታ ፈልጎታል፡፡ ነገር ግን ምንም ነገር አላገኘም፡፡
በቅርብ አካባቢ ወዳለው ገበያ ሄዶ ገንዘብ ለማግኘት ወሰነ፡፡
አቡላ ወደ ገበያ እየሄደ እያለ አባቱ አዩት፡፡
"ልጄ ለምን ወደ ገበያ እንደምትሄድ አውቃለሁ፡፡ አሁን ተመልሰህ ግባ እና በመጻሕፍቱ ውስጥ ገንዘቡን ፈልገው" አሉት፡፡
አቡላ ግራ ገባው፡፡ ቢሆንም ወደ ቤት ገባ እና መጽሐፉ ውስጥ ገንዘቡን ፈለገው፡፡
እናቱ ደብቀው ያስቀመጡትን ገንዘብም አገኘው፡፡
በሚቀጥለው ቀን እንደገና በመጻሕፍቱ ውስጥ መፈለግ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ተደብቆ ያገኘው ነገር የለም፡፡
በመጻሕፍቱ ውስጥ ለምን ገንዘብ እንደሌለ ለመጠየቅም ወደ አባቱ ዘንድ ሄደ፡፡
አባቱ ፈገግ አሉና "የኔ ልጅ ብስኩት የምትገዛበት በቂ ገንዘብ ትፈልጋለህ?" አሉት፡፡
አቡላም "አዎ አባዬ" አለ፡፡
አባቱ "በጥሞና አዳምጠኝ፡፡ መጻሕፍትን አንብብ፡፡ ትምህርትህን ተከታተል፡፡ ከመጻሕፍት ሽልማት ታገኛለህ፡፡ አታቋርጥ" አሉት፡፡
"ግን እኮ አባዬ፣ ማንበብ አስቸጋሪ ሥራ ነው፡፡ መጻሕፍትም ደባሪ ናቸው" ሲል አቡላ መለሰ፡፡
ለአፍታ፣ የአቡላ አባት ዝም አሉ፡፡ ልጃቸውን እንዴት ማበረታታት እንዳለባቸው አሰላሰሉ፡፡
ከዚያም ለአቡላ "እስኪ በአንድ ላይ እናንብብ፡፡ ከመጻሕፍት ውስጥ እንዴት ገንዘብ እንደሚገኝም ላሳይህ" አሉት፡፡

