

የተከፋች ዝንጀሮ ለብዙ ጊዜ በሚዋ ጫካ ውስጥ ኖራለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ሁልጊዜ ትወልዳለች፤ ግልገሏ ይሞትባታል፡፡
ግልገሎቿን የማጣቷ ሀዘን ወደ ዛፍ ላይ ዘልላ እንዲትወጣ እና እንዲትወርድ አድርጓታል፡፡ ወደ አንዱ ቅርንጫፍ ዘላ ትወጣለች፣ ከዚያም ወደ ሌላው ትሻገራለች እና "ክዊ! ክዊ! ክዊ!" እያለች ታለቅሳለች፡፡
ዝንጀሮዋ ሁልጊዜም ያዘነች ናት፡፡ ሌሎች ዝንጀሮዎችን ከግልገሎቻቸው ጋር ስታይ ይበልጥ ትከፋለች፡፡
ሃዘንተኛዋ ዝንጀሮ ከቀርንጫፉ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ሳትነሣ ቀናት አለፉ፤ ደጋግማ ደጋግማ አለቀሰች፡፡
ከዚያም እንደገና ወለደች፡፡ ሰዎች ሲያዩት ያሳድግህ እያሉ እንዲመርቁት፣ ግልገሏን ወደ መንግድ ዳር ለመውሰድ ወሰነች፡፡
ዝንጀሮዋ ከዛፉ ላይ ወረደችና ግልገሏን ከመንገድ ዳር አስቀመጠችው፡፡ በዚያን ሰዓት አዳኙ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነበር፡፡ በመንገዱ ዳርቻ ላይ ግልገሉን ተኝቶ አየው፡፡
አዳኙ ግልገሉን አቅፎ ወደ ቤቱ ወሰደው፡፡ እቤቱ ሲደርስም ሦስቱም ወንዶች ልጆቹ ግልገሉን ለመያዝ ፈለጉ፡፡
የአዳኙ ልጆች "ወደላይ አጉነው! ወደ ታች አንጥረው! ወደ እኔ ወርውረው! ለእሱ አቀብለው!" በሚል ዝማሬ ይጫወቱበታል፡፡
እናትዮዋ ዝንጀሮ፣ ሦስቱ የአዳኙ ልጆች በግልገሏ ሲጫወቱ በዛፎቹ መሀል ተደበቀች፡፡ እያየቻቸው ነበር፡፡ ይኸኛው ግልገል ደግሞ እንደነዚያኞቹ እንዳይሞት ፈራች፡፡
ከዚያም የአዳኙ ሚስት መጣች እና ልጆቿ በግልገሉ ሲጫወቱበት አየች፡፡ "ተጠንቀቁ! ትጥሉታላችሁ! ወደኔ አምጡት!" አለቻቸው፡፡
የልጆቹ እናት ግልገሉን ተቀብላ በክንዶቿ አቀፈችው፤ መረቀችው!
የአዳኙ ሚስት ግልገሉን ለቀቀችው፡፡ ዝንጀሮዋም ልጇን አንሣች፡፡ ይዛው ወደ ጫካው ተሰወረች፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሁሉም ልጆቿ አደጉላት፡፡

