የደብረ ብርሃን ፈረሶች
Mezemir Girma
Yirgalem Birhanu

ቻለው የጋሪ ፈረስ ነው፡፡

በደብረ ብርሃን ኮረኮንች መንገዶች ከባባድ ሸክም በመሸከም ህይወቱን ይገፋል፡፡

ከማለዳ እስከ ምሽት ድረስም ይሰራል፡፡

1

ቻለው በቂ የእረፍት ጊዜ አያገኝም፡፡

በቂ ምግብም አያገኝም፡፡

ጋሪ ነጂው ቻለውን ፈጥኖ እንዲሄድለት በአለንጋ ይገርፈዋል፡፡

2

አንድ ቀን ሁሉም የጋሪ ነጂዎች ለቀብር ተሰባሰቡ፡፡

የጋሪ ፈረሶቹም ከቀብር ቦታው አቅራቢያ ባለ መስክ ላይ ሳር እየጋጡ ነበር፡፡

ፈረሶቹ ስለሚደርስባቸው ሰቆቃ ሁሉ መነጋገር ጀመሩ፡፡

3

‹‹ልጓሜ አይስማማኝም፡፡ ጥብቅ ያለ ስለሆነ ቆዳዬን ይቆርጠኛል›› አለ አንደኛው ፈረስ፡፡

‹‹እኔም፡፡ እኔም›› ሲል ተናገረ ሌላኛው በመስማማት፡፡

4

አንድ በዕድሜ የገፋ ፈረስ ‹‹ሸሆናዬ ላይ በሚስማር በሚመቱብኝ ጫማዎች ምክንያት አንካሳ ልሆን ምንም አልቀረኝ›› አለ፡፡

በርካታ ፈረሶች በመስማማት ራሳችን ነቀነቁ፡፡

5

‹‹ከባባድ ስራ ብንሰራም ብዙዎቹ ባለቤቶቻችን አያያዛቸው መጥፎ ነው፡፡ አብዛኞቹ እኛን እንዴት እንደሚይዙ አያውቁበትም›› አለ ቻለው፡፡

ፈረሶቹም በአንድነት ተስማሙ፡፡

6

‹‹የተሻለ ሕይወት እንፈልጋለን፡፡ አድማ እናድርግ!›› በማለት ቻለው አወጀ፡፡ ሁሉም ፈረሶች በደስታ ጮሁ!

ጋሪ ነጂዎቹም ለለውጥ እስከሚዘጋጁ ድረስ ፈረሶቹ በዚያው ሜዳ ላይ ለመቆየት ወሰኑ፡፡

7

ጋሪ ነጂዎቹ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገባቸው፡፡

‹‹ሌላ ፈረስ እቀይራለሁ›› በማለት አንደኛው ነጂ በጉራ ተናገረ፡፡

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ነጂዎች ኑሯቸውን ለመግፋት ፈረሶቹ ያስፈልጓቸው ነበር፡፡

8

ስለ አድማው ሁኔታ ለመነጋገር ጋሪ ነጂዎቹ ስብሰባ አካሄዱ፡፡ ለረጅም ጊዜ ተከራከሩ፡፡

‹‹ፈረሶቹ ትክክል ሳይሆኑ አይቀሩም›› አለ አንደኛው ሰውዬ፡፡

‹‹ከዚህ በላይ ምን እናድርጋቸው?›› በማለት አንድ ሌላ ሰው ጠየቀ፡፡

9

የፈረሶቹ አድማ ከደብረ ብርሃን ከተማ ወደ መላው ኢትዮጵያ ተዛመተ፡፡

ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ፈረሶች እምቢተኝነታቸውን አሳዩ፡፡

ባለቤቶቻቸውን ‹‹የእስካሁኑ ይበቃናል! በአግባቡ ያዙን!›› አሏቸው፡፡

10

በዚህም ምክንያት የጋሪ ነጂዎቹ ለመለወጥ ተገደዱ፡፡

አሰራራቸውን ለማሻሻልና ሁሉንም ፈረሶች በተሻለ ሁኔታ ለመያዝ ተስማሙ፡፡

ፈረሶችን እንዴት እንደሚንከባከቡና ጤናቸውን እንደሚጠብቁ ተማሩ፡፡

11

ቀስ በቀስም የፈረሶቹ ሕይወት እየተሻሻለ ሄደ፡፡

በቂ ምግብና እረፍት አገኙ፡፡ ልጓሞቻቸው በልካቸው ተሰሩላቸው፡፡ ለእግራቸው የተሻሉ ጫማዎችን አገኙ፡፡

በዕድሜ የገፋው ቻለውም የሁሉም ፈረሶች ጀግና ሆነ!

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
የደብረ ብርሃን ፈረሶች
Author - Mezemir Girma
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Yirgalem Birhanu
Language - Amharic
Level - First paragraphs