የአቶ ሞታኡንግ ሲሶዎች
Lindiwe Tshabalala
Marleen Visser

በሲያፉንዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የረፍት ሠዓት ነው፡፡ ኖምሳ፣ ጃቡና ዞድዋ የሚባሉ ልጆች ዛፍ ጥላ ስር ምሳ ለመብላት ተቀምጠዋል፡፡ ዛሬ ኖምሳና ዞድዋ ምግብ ከቤታቸው አምጥተዋል፡፡ ጃቡ ከአቶ ማኪዜ ሱቅ የገዛውን ኮታ እየበላ ነው፡፡

1

‹‹ምምም… ይህ አይብ ቅባት አለው! የአቶ ማኪዜ ኮታ አሪፍ ነው!›› ይላል ጃቡ ጣቶቹን እየላሰ፡፡ ተቦጋ በአቅራቢያው ስለተቀመጠ ጃቡ የሚናገረው ይሰማዋል፡፡ ጆሮውን ማመን አልቻለም! ስለሆነም ተቦጋ ‹‹የአቶ ማኪዜ ኮታ አይብ አለው እያልከኝ ነው? የማኪዜ ኮታ የተሻለ ነው አልክ? እየቀለድክ ነው እንዴ?›› ሲል ጠየቀው፡፡

2

‹‹ሃሃሃ! አቶ ማኪዜን አታውቀውም! አሰራሩን ቀይሯል፤ ይህ ኮታም ለዚያ ምስክር ነው›› አለ ጃቡ ወደ ኮታው እየጠቆመ፡፡ ኮታው በድንች ጥብስ፣ በስጋና በቅመም የተሞላና በሚያጓጓ አይብ የተሸፈነ ነው፡፡ ተቦጋ ጎመጀ፡፡ ወዲያውም ሴሎ ምሳውን ይዞ ሲደርስ ተቦጋ ‹‹ሰላም ነው ሴሎ፤ ይህን ኮታ እየው!›› አለው፡፡

3

ጃቡ የሴሎን ፊት አይቶ ‹‹ለምንድነው ሃሳብ የገባህ!›› ሲል ጠየቀው፡፡ ሴሎ ኮታውን ከጃቡ ኮታ ጎን አስቀመጠው፡፡ ‹‹እኔ የገዛሁት ከአቶ ሞታኡንግ ነው፡፡ የኮታዎቹም መጠን እኩል ነው፡፡ የኔ ግን ማባያ ያንሰዋል!›› ‹‹አዎ›› አለ ኖምሳ ‹‹ለዚያ ነው ብዙ ልጆች ከአቶ ማኪዜ ሱቅ እየገዙ ያሉት፡፡››

4

‹‹እና አቶ ማኪዜ ተቀይሯል? አንድን ዳቦ አምስት ቦታ እየቆረሰ ነበር ኮታ የሚሰራው!›› አለ ተቦጎ፡፡ ‹‹አሃ!›› መለሰች ኖምሳ ‹‹ያማ ጭራሽ ኮታ አልነበረም!›› ‹‹ለምንድነው ኮታ ያልሆነው?›› ሲል ጠየቀ ሴሎ፡፡

5

‹‹ሃ ሴሎ!›› ብላ ሳቀች ኖምሳ፡፡ ‹‹አስተማሪያችን ስለ ክፍልፋዮች ያስተማሩንን አታስታውስም? አንድን ዳቦ ወደ አምስት እኩል ክፍልፋዮች መቆራረጥ ሩብ አያመጣልንም፡፡ አንድ አምስተኛ ነው እንጂ›› ስትለው ሴሎ አሰበና ‹‹አስታውሳለሁ! አንድ ሙሉ ለ5 እኩል ክፍፋዮች ከተካፈለ የሙሉው 1/5ኛ ነው፡፡ አንድ ሙሉ ለ4 እኩል ክፍልፋዮች ከተከፋፈለ ደግሞ የሙሉው 1/4ኛ ይሆናል፡፡››

6

ዞድዋ ‹‹ግን ስሙኝ እስኪ፤ የአቶ ሞታኡንግ ኮታዎች ምን በጃቸው? የአንድ ዳቦ ሩብ ናቸው፤ ይሁን እንጂ ከአቶ ማኪዜ ኮታ ያነሱ ናቸው›› በማለት አቋረጣቸው:: ጃቡ ከስተር ብሎ ለቡድኑ ‹‹ሞታኡንግ ችግር ውስጥ ገብቶ ከንግድ ቢወጣ ማኪዜ ምንም ዓይነት ፉክክር አይኖርበትም፡፡ ማኪዜ ቢሰስትና ወደ ዱሮው መንገዱ ቢመለስስ?›› አለ፡፡

7

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ አቶ ሞታኡንግ በረፍት ሰዓት ምሳ ለመሸጥ እየተዘገጃጀ ነው፡፡ ተጨንቋል፡፡ በሂደት የገዢው ተማሪ ቁጥር እየወረደ መጣ፡፡ አቶ ሞታኡንግ ራሱን ‹‹ለምንድነው ሁሉም ወደ ማኪዜ የሚጎርፉት? እኔ የማላደርገው እሱ የሚያደርገው ነገር ምንድነው? ተመሳሳይ ኮታ በአንድ ዓይነት ዋጋ እየሸጥን ያለን ይመስለኝ ነበር›› በማለት ጠየቀ፡፡

8

ጃቡ ከማኪዜ ሱቅ ሲመለስ በአቶ ሞታኡንግ ሱቅ አለፈ፡፡ ሞታኡንግ ልጁን ጠራው፡፡ ‹‹ሰላም ነው ጃቡ፤ እንዴ አለህ? ካየሁህ ቆየሁ›› አለው፡፡ የአቶ ሞታኡንግ ዓይኖች በጃቡ ላይ ሳይሆን ጃቡ በያዛቸው ኮታዎች ላይ ተተከሉ! ኮታው የበለጠ ድንች ጥብስ፣ አይብ፣ ስጋና ቅመም እንዳለው ተረዳ! አቶ ሞታኡንግ የማኪዜን ሚስጥር ስላወቀ ፈገግ አለ፡፡

9

በቀጣይ ጊዜ ኖምሳና ዞድዋ ኮታ ሲገዙ ማኪዜ ስጦታ ሰጣቸው፡፡ ‹‹አንዴ ጠብቁኝ፤ ያልተጠበቀ ነገር ላደርግላችሁ ነው፡፡ በቅርቡ በሱቄ ፍራፍሬ መሸጥ እጀምራለሁ፡፡ እንካችሁ እነዚህን ጣፋጭ ፖሞች በነጻ ቅመሷቸው፡፡ ለጓደኞቻችሁም አካፍሏቸው፡፡›› አላቸው፡፡

10

ልጃገረዶቹም ተፍነከነኩ፡፡ ‹‹እናመሰግናለን አቶ ማኪዜ!›› አሉ ሁሉም በአንድነት፡፡ ፖሞቹንም ለጃቡ፣ ቶቦጎ እና ሴሎ ለማካፈል ወስነው ሊፈልጓቸው ወደ ጓሮ አቀኑ፡፡

11

ዞድዋ ለወንዶቹ ልጆች ‹‹አቶ ማኪዜ ፖም እንድንካፈል ሰጥቶናል፡፡ ወደፊት መሸጥ እጀምራለሁ ብሏል›› አለች፡፡ ኖምሳም ፖሞቹን ማስደገፊያ ላይ አስቀምጣ ለቆጠራ አዘጋጀቻቸው፡፡ ‹‹እናም›› አለ ቶቦጎ ‹‹እያንዳንዳችን እኩል ይደርሰናል፡፡ አንድ ፖም ታዲያ ይተርፋል፡፡››

12

‹‹ቀሪውን ፖም ሦስት እኩል ቦታ እንቁረጠው›› በማለት ጃቡ ሐሳብ አቀረበ፡፡ ‹‹እነዚያ ሦስት እኩል ክፍሎች ምን ይባላሉ?›› አለች ኖምሳ ለራሷ፡፡ ‹‹ሲሶዎች! ፖሙን ወደ በሲሶ ቁረጠው›› አለ ሴሎ በኩራት፡፡

13

‹‹አይ የተረፈውን ፖም ለሒሳብ መምህራችን እንስጣቸው!›› አለ ዞድዋ፡፡ ጓደኛሞቹም ፖሙን ከረፍት በኋላ ለመምህርት ኒኮዚ መስጠት ጥሩ ጥቆማ እንደሆነ ተስማሙ፡፡

14

በመጪው ሳምንት ጃቡና ኖምሳ በረፍት ሰዓት ዞድዋን እየጠበቋት ነው፡፡ ዞድዋ ኮታዋን ይዛ ደረሰች፡፡ ‹‹እዩ፣ ሞታኡንግ ወደ ስራ ተመልሷል!›› አለቻቸው፡፡ ዞድዋ ኮታዋን ማስደገፊያው ላይ አድርጋ ሦስቱ ኮታውን አወዳደሩ፡፡ ‹‹አቤት!›› አለ ጃቡ ‹‹ያ ኮታ ከሩብ በላይ ነው! እና እነዚያን የድንች ጥብሶች እዩአቸው!››
‹‹ይህም ተጨማሪ ወጪ እንደለው እወራረዳለሁ? አቶ ሞታኡንግ ግን እንዴት ነው የሚያተርፈው?›› ስትል ኖምሳ በጥርጣሬ
ጠየቀች፡፡

15

ከረፍት በኋላም ወደ ክፍል እያቀኑ ሳለ ዞድዋ አቶ ሞታኡንግ ሱቅ ላይ የተለጠፈውን ማስታወቂያ እንዲያነቡ ጓደኞቿን ወሰደቻቸው፡፡ ጃቡና ኖምሳ በማስታወቂያው ላይ የሚከተለውን ሲያነቡ ዓይኖቻቸውን ማመን አልቻሉም፡- ኮታችሁን ተመገቡ! ሦስት ብር ብቻ ያስጨምራል! ሲሶውን ከተጨማሪ ድንች ጥብስና ቅመም ጋር፡፡ ከፈለጉ ከስጋ ወይም አይብ ጋር!

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
የአቶ ሞታኡንግ ሲሶዎች
Author - Lindiwe Tshabalala, African Storybook
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Marleen Visser
Language - Amharic
Level - Read aloud