አቤልና የእህቱ አሻንጉሊት
Eyobi Kitaw
Jesse Breytenbach

አቤል የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ጋሪ ሰራ፡፡ ለአዲሷ ጋሪው ግን ነጂ አልነበረውም፡፡ እህቱን ሜሪን ‹‹ጋሪዬን የሚነዳልኝ ሰው እፈልጋለሁ፡፡ እባክሽ አሻንጉሊትሽን ስጪኝ›› አላት፡፡

1

ሜሪ ግን ‹‹አይሆንም፣ አሻንጉሊቴ ታስፈልገኛለች›› ስትል መለሰችለት፡፡ ሜሪ አሻንጉሊቷን እንደማትሰጠው ሲያውቅ አቤል ተናደደ፡፡ አሻንጉሊቷን ይዞ ሳባት፡፡ ሜሪ የአሻንጉሊቷን ሌላኛውን እጅ ይዛ ትጎትት ጀመር፡፡ አቤልም ሜሪም ይጎትቱ ጀመር፡፡ የአሻንጉሊቷ እጅ ተገነጠለ!

2

ሜሪ እያለቀሰች ወደ እናቷ በሩጫ ሄደች፡፡ ‹‹እማማ እዪ›› አለች፡፡ ‹‹አቤል የአሻንሊቴን እጅ ገነጠለብኝ፡፡ አሻንጉሊቴ እሱ ጋሪ ላይ እንድትቀመጥ ጠየቀኝ፡፡ እኔ ግን እጫወትባታለሁ አልኩት፡፡›› እናትዬዋም ‹‹አቤል አጥፍቷል›› አለቻት፡፡

3

እናትዬዋ ልጇን እንዴት አድርጋ የእህቱን አሻንጉሊት እንዳይነካባት እንደምታስተምር አሰበች፡፡ አንድ ሐሳብ መጣላት፡፡ ወደ አንዲት ዶክተር ጓደኛዋ ዘንድ ሄዳ ‹‹እባክሽ እርጅኝ›› ስትል ተማጸነቻት፡፡ ዶክተሯም ‹‹ወዳጄ፣ ምን ልርዳሽ?›› ስትል መለሰችላት፡፡

4

እናትዬዋም ‹‹ልጄ አቤል ባልጎብኛል፡፡ የእህቱን አሻንጉሊት እጅ ገነጠለባት፡፡ ያንን ማድረግ አልነበረበትም፡፡ ነገ አሻንጉሊቷን ወዳንቺ አምጥቶ እጇን እንዲያሰራ እነግረዋለሁ›› አለቻት፡፡

5

‹‹ለምትሰሪለት ስራ እንከዲፍልሽ ንገሪው፡፡ ገንዘብ ስለሌለው ትልቋን መኪናሽን እንዲያጥብ ንገሪው›› አለች እናትዮዋ፡፡ ዶክተሯም ሳቀችና ‹‹እ - እ!! ጥሩ ነገር አመጣሽ›› አለቻት፡፡

6

የአቤል እናት ወደ ቤቷ ተመልሳ ሄደች፡፡ አቤልንም ‹‹ሲያምህ ወይንም ስትጎዳ የት ነው የምትሄደው?›› ስትል ጠየቀችው፡፡ ‹‹ስታመም ወይንም ስጎዳ ወደ ሐኪም ቤት እሄዳለሁ›› ሲል መለሰላት፡፡ እናትዬዋም ‹‹አሻንጉሊቷን አበላሽተሃታል፤ በል አሁን ወደ ሐኪም ዘንድ ውሰዳት›› አለችው፡፡

7

አቤልም አሻንጉሊቷን ወደ ሐኪሟ ይዞ ሄደ፡፡ ‹‹ይቺ አሻንጉሊት በጣም ተጎድታብኛለች፡፡ እናቴ ወዳንቺ እንዳመጣት አዛኝ ነው፡፡ ዶክተር እጇን ልትቀይሪላት ትችያለሽ?›› አላት፡፡ ዶክተሯም እንደምታስተካክልለት ነገረችው፡፡ አዲስ እጅም ሰራችላት፡፡

8

ዶክተሯም ለአቤል ‹‹አሻንጉሊትህ እጇ ተሰርቶላታል፡፡ እንግዲህ ልትከፍል ይገባሃል፡፡ ምን ያህል ገንዘብ አለህ? አለችው፡፡ አቤልም ‹እባክሽ ዶክተር፣ ምንም ገንዘብ ስለሌለኝ ልከፍልሽ አልችልም›› አላት፡፡

9

ዶክተሯም ‹‹እና! ምንም ገንዘብ የለህም? ያ ትልቁ መኪናዬ ይታይሃል? ቆሽሾብኛል! እሱን ካጸዳህ ከፈልከኝ ማለት ነው›› አለችው፡፡
አቤል ውሃ በባልዲ እና መጥረጊያ ጨርቅ ይዞ ስራውን ጀመረ፡፡ ያንን ቆሻሻ መኪና ለማጽዳትም ረጅም ጊዜ ወሰደበት፡፡

10

ከዚያም አቤል አሻንጉሊቷን ለሜሪ ይዞላት ሄደ፡፡ በጣም ተደስታ ለአቤል ‹‹ጥሩ ወንድሜ ነህ፡፡ አሻንጉሊቴን ስላስተካከልክልኝ አመሰግናለሁ›› አለችው፡፡
‹‹እህቴ ተናድጄ ስላስከፋሁሽ ይቅርታ›› አላት አቤል፡፡

11

ከዚያን ቀን ጀምሮ አቤል የእህቱን እቃዎች ነክቶ አያውቅም፡፡ በተቻለው መጠን ከእህቱ ጋር ላለመጣላት ይሞክራል፡፡
አቤል የዶክተሯን ትልቅና ቆሻሻ መኪና ማጠቡ የወሰደበትን ጊዜ ያስታውሳል፡፡ በንዴት እቃዎችን ማበላሸት ብዙ ጣጣ እንደሚያመጣ ገብቶታል፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
አቤልና የእህቱ አሻንጉሊት
Author - Eyobi Kitaw
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Jesse Breytenbach
Language - Amharic
Level - First paragraphs