

ከእለታት በአንዱ ቀን ጥንቸል በጣም ይርባትና ምግብ ፍለጋ ትወጣለች፡፡ በመንገድ ላይም ስትጔዝ ማሰሮ ሙሉ ማር ተሸክማ ስትሄድ የነበረች ዝሆን ታገኛለች፡፡ ከዚያም ‹‹እባክሽ ዝሆን በጣም ስለደከመኝና መራመድ ስላቃተኝ ጀርባሽ ላይ ወጥቼ እንድጔዝ ፍቀጅልኝ›› አለቻት፡፡
ዝሆንም ጥንቸል ስታነክስ በማየቷ ታዝንና በሃሳቧ ትስማማለች፡፡ ጥንቸልም ዝሆኗ ጀርባ ላይ በፍጥነት ወጣችና ከማሰሮው ውስጥ ቀስ እያለች ማር እያወጣች መላስ ጀመረች፡፡
ጥንቸል ማሩን በምትልስበት ወቅትም ማሩ ከእጇ እያመለጣት ዝሆኗ ገላ ላይ መንጠባጠብ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜም ዝሆኗ በገላዋ ላይ ምን እየፈሰሰ እንደሆነ ጥንቸልን ስትጠይቃት፤ ጥንቸልም የቁስሏ ደም እንደሆነ ነገረቻትና ዝሆን መንገዷን ቀጠለች፡፡
በመንገዳቸውም ላይ አንድ ጎሽ ከወንዝ ዳር ቆሞ ውኃ ሲጠጣ ያገኛሉ፡፡
ጥንቸልም ከዝሆን ጀርባ በፍጥነት ወረደችና “ከሁለታችሁ ግን ማነው በጣም ጠንካራ” ብላ ዝሆንንና ጎሽን ጠየቀች፡፡
ዝሆንና ጎሽም መጨቃጨቅ ጀመሩ፡፡ ዝሆን ‹‹እኔ በጣም ጠንካራ ነኝ›› ስትል፤ ጎሽም ‹‹እኔ ነኝ በጣም ጠንካራ›› በማለት መለሰች፡፡
ጥንቸልም “ቆይ ማን በጣም ጠንካራ እንደሆነ የምናውቅበት ጥሩ ሃሳብ አለኝ፤ የትም ሳትሄዱ እዚሁ ጠብቁኝ” ብላ እየሮጠች ሄደች፡፡
ጥንቸልም ረጅም ገመድ ይዛ ተመለሰች፡፡ ከዛም አንዱን ጫፍ ዝሆኗ ወገብ ላይ አሰረችና ወደኋላ እንድትርቅ አደረገች፡፡
ጥንቸል ሌላኛውን የገመድ ጫፍ በጎሿ ወገብ ላይ አሰረችና ጎሿን ወደ ወንዙ ተጠግታ እንድትቆም አደረገች፡፡
ጥንቸልም ሮጣ ዛፍ ላይ ከተደበቀች በኋላ ጮክ ብላ "ለመጎተት ተዘጋጅ! አንድ! ሁለት! ሦስት!" በማለት ቆጥራ ጉተታዉን አስጀመረች፡፡
ጎሿና ዝሆኗ መጎተት ጀመሩ፡፡ መጀመሪያ ዝሆን ጎሿን ጎተተቻት፡፡
ከዛ ደግሞ ጎሿ ዝሆኗን ጎተተች፡፡ ሁልቱም ሲጔተቱ ቆዩ፤ ነገር ግን ማናቸውም ሊያሸንፉ አልቻሉም፡፡
እነሱ ሲጔተቱ ጥንቸል ከተደበቀችበት ስፍራ ሆና የዝሆንን ማር ትልሳለች፡፡
ማሩንም ልሳ ስትጨርስ በጎሿ በኩል ያለዉን ገመድ ቀስ ብላ ቆረጠችው፡፡
ዝሆንም በጣም እየጎተተች ስለነበር ተወርውራ ወደሗላ ወደቀችና ከዛፉ ጋር ተጋጨች፡፡
ጥንቸልም ወደ ጎሽ ሄደችና “አንቺ በጣም ጠንካራ ነሽ፤ ዝሆንን አሸነፍሻት” በማለን አደነቀቻት፡፡

