

በጥንት ዘመን እንስሶች ማውራት ይችሉ ነበር፡፡ በዚህ ዘመንም አንዲት ጥንቸልና አንድ ጅብ በአንድ ላይ ይኖሩ ነበር፡፡
ሁለቱ እንስሳት በጣም የቅርብ ጓደኞች በመሆናቸው የተነሳ ሁሉን ነገር አብረው ነው የሚያከናውኑት፡፡ ምግባቸውንም በአንድ ላይ ነው የሚፈልጉት፡፡
ጥንቸል በጣም ጎበዝ ነበረች፡፡ ሁሌም ከሰነፉ ጅብ በተሻለ ብዙ ምግብ የምታከማቸው ጥንቸል ነበረች፡፡
ጅቡ ስራ ላይ በጣም ሰነፍ ቢሆንም ምግብ መብላት ግን በጣም ይወድ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በተለያየ መልኩ ምግባቸውን አድነው ቢያመጡም ምግባቸውን ግን የሚያስቀምጡት በአንድ ላይ ነበር፡፡
ጥንቸል ብልሃቷን በመጠቀም ቶሎ ቶሎ የሚበላ ነገር ታመጣለች፡፡ ካደነችው ምግብ ውስጥም ወደ ጅብ ጋር ከመሄዷ በፊት በመንገድ ላይ ጥቂት ጥቂት ትበላለት ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ድርቅ ይከሰትና በዚህ ጊዜ ለሁለቱም የሚሆን በቂ ምግብ ማግኘት አቃታቸው፡
ጅቡም ምግብ መፈለጉን አቁሞ ጥንቸል የምታመጣውን ትንሽ ምግብ መጋራት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ጥንቸል በጣም ይርባትና ይከፋት ጀመር፡፡ ጥንቸል ምግብ አጥታ ወደቤት የተመለሰች ግዜ በጣም ተስፋ ትቆርጥ ነበር፡፡
ጅቡም ምንም ፀባዩን ማስተካከል አልቻለም፡፡ ሁሌም ጥንቸል የምታመጣው ምግብ ብቻ መጠበቁንና ጥገኝነቱን ቀጥሎበታል፡፡ ጅቡ ያለምንም እገዛ መመገቡ የጥንቸልን ህይወት በጣም እያከበደው መጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ጥንቸል ሰነፉን ጅብ እንዴት እንደምታስወግድ እቅድ መንደፍ ወሰነች፡፡
አንድ ቀን ጥንቸል ጅቡን በጠዋት ቀሰቀሰችው፡፡ ከዛም እንዴት መኖር እንዳለባቸው ለመወያየት ከአንድ ዛፍ ስር ቆሙ፡፡
ምንም እንኳን ስለጉዳዩ ቢወያዩም በሀሳብ ሊስማሙ አልቻሉም፡፡ ጅብ ለሽንፈቱ ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው እንደ ጥንቸል ፈጣን አለመሆኑንና ሮጦ በቅልጥፍና ማደን አለመቻሉን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአደኑን ስራ ጥንቸል እንድታከናውን በመንገር እሱ ግን ማንኛውንም የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት እንደሚችል ገለፀ፡፡
አንድ ምሽት ላይ ለአደን በምትንቀሳቀስበት ወቅት አንድ በደንብ ያልበሰሉ ወይኖች የሞሉበት ዛፍ ተመለከተች፡፡ ከአንድ ዛፍ ስር ቁጭ ብላም እንዴት አድርጋ እንደምትመገብና እንዴት አድርጋ ደግሞ ወደ ቤት መውሰድ እንደምትችል እቅድ ማውጣት ጀመረች፡፡ መናፈሻው በአጥር የታጠረ ስለሆነ ይህን ለማድረግ ከባድ እንደሚሆንባት ገምታለች፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ ጥንቸሏ ዛፉ ስር መድረስ ቻለች፡፡
ከዚያም ዛፉ ላይ በመውጣት የቻለችውን ወይን ወደ መሬት አራገፈች፡፡ በጣም ስለራባትም ዛፉ ላይ የቀረውን ወይን ተመገበች፡፡ ከዛፉም በመውረድ ያራገፈችውን ወይን በመሰብሰብ ይዛ ወደ አመጣችው ቅርጫት ውስጥ ከተተችና ለመሸከም ስትሞክር በጣም ስለጠገበች መያዝ አቃታት፡፡ ስለዚህ ትንሽ እረፍት ማድረግ እንዳለባት ወስና ለማረፍ ሞከረች፡፡ ነገር ግን በዚያው እንቅልፍ ይዟት ሄደና በተኛችበት የወይኑ ባለቤት አገኛት፡፡ ሰውየውም ጥንቸልን ከያዛት በኋላ እንዳታመልጥ በረጅም ገመድ ካሰራት በኋላ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ፡፡
ገመዱም እጅግ በጣም ረጅም በመሆኑ እንደታሰረች እስከ መኖሪያ ብቷ ድረስ መጓዝ አስቻላት፡፡ እዚያ እንደደረሰች ጓደኛዋን ጅብን እንዲህ ስትል አሞኘችው፡- ‹‹ብታይ ጫካው ውስጥ በጣም ትልቅ ድግስ አለ፡፡ ድግሱ ላይ የሚኬደው ደግሞ በገመድ በመታሰር ነው፡፡ ስለዚህ እኔም በልቼ የመጣሁት ገመዱን አስሬ ነው፡፡ እንግዲህ አንተም ገመዱን እሰርና ቦታው እንዳይጠፋህ የድግሱ ቦታ ድረስ ገመዱ ይመራሃል፡፡ ተከትለህ ሂድና እስክትጠግብ ድረስ መመገብ ትችላለ›› በማለት አሞኘችው፡፡
አያ-ሞኙ ጅብም ገመዱን ከጥንቸል ላይ ፈታላትና እራሱን በደንብ አሰረ፡፡ ከዛም ገመዱን እየተከተለ ሲጓዝ ትልቅ ቢላ ይዞ በጉጉት እስኪመጣ ሲጠባበቅ ወደነበረው የመናፈሻው ባለቤት ጋር ይደርሳል፡፡ ሰውየውም ጅቡን በቶሎ አረደውና ስጋውን ለውሻዎቹ መገባቸው፡፡ ቆዳውን ደግሞ የወፍ ማስፈራሪያ እንዲሆን መናፈሻው ውስጥ በእንጨት ላይ ሰቀለው፡፡

