እረኛውና የልብ ጓደኛው
Biniam Asfaw
Isaac Okwir

ታሪክ በረግረግ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ በመንዝ፣ ሰሜን ሸዋ፣ኢትዮጵያ ይገኛል፡፡

1

ታሪክ ቡቼ የተባለ ውሻ ነበረው፡፡ ቡቼ ባለበት ታሪክም ይገኝ ነበር፡፡ ታሪክ እናቱ ምግብ ስትሰጠው እንኳን ለቡቼ ያካፍለው ነበር፡፡

2

ታሪክና የክፍል ጓደኛው በድሉ ትምህርት በሌለባቸው ጊዜ በጎች ያግዱ ነበር፡፡

አንድ ቅዳሜ ጠዋት ታሪክና በድሉ በጎቻቸውን ወደጋራ የግጦሽ መስካቸው ነዱ፡፡

3

ማጥናት ይችሉም ዘንድ ደብተሮቻቸውን ይዘዋል፡፡ መንገዳቸው ላይ በድሉ ‹‹አንተ! ከጥናት በፊት አእምሯችንን ለማዝናናት አንድ አፍታ ኪሳራ እንጫወት›› አለው፡፡
ታሪክም ‹‹አይ ተው! ማጥናት ብንጀምር ነው የሚሻለን!›› ሲል መለሰለት፡፡

4

‹‹አይዞህ! ጥናት አሁኑኑ እንጀምራለን፡፡ እንጫወት?›› ሲል በድሉ ለመነው፡፡ በመጨረሻም ኪሳራ ተጫወቱ፡፡

(ኪሳራ፣ ተጫወቾቹ ተራ እየገቡ ጠፍጣፋ ድንጋዮች ወይንም ሳንቲሞች ከአንድ ሜትር ተኩል ገደማ ርቀት ላይ እየወረወሩ ትንሸ ጉድጓድ ውስጥ በማስገባት የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡)

5

ሳያውቁት ለሁለት ሰዓት ገደማ ተጫወቱ፡፡

በጎቻቸው ሁሉ ጠፉ፡፡ ሲፈልጉ የትም ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ በጎቻቸውን ፍለጋ በየቦታው ተሯሯጡ፡፡

6

ከርቀት አንድ ቀበሮ በጎቻቸውን ሲያባርራቸው አዩት! ታሪክና በድሉ እዚያ ደርሰው የታሪክን በግ እንደበላበት አዩ፡፡ ታሪክ ማልቀስ ጀመረ፡፡ አባቱ እንደሚገርፈው አውቆታል፡፡

7

በድሉ በጎቹን ወደ ቤት ሲወስድ ታሪክ ግን አልሄደም፡፡ ከቤቱ ብዙም የማይርቅ ቦታ ላይ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ላይ ወጥቶ ምሽቱን ለማሳለፍ ወሰነ፡፡
አንድ ቅርንጫፍም ላይ ተኛ፤ ቡቼ በበኩሉ ከበታቹ መሬት ላይ ተኛ፡፡

8

እኩለ-ሌሊት ላይም ታሪክን የጅቦች ጩኸት ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡ ከዛፉ ቅርንጫፍ ላይ እወድቃለሁ ብሎ ፈራ፡፡

9

ታሪክ ከበታቹ የእንስሳት ድምጽ ቢሰማም ምን ዓይነት እንስሳት መሆናቸውን ለማወቅ ጨለማ በመሆኑ ምክንያት አልቻለም ነበር፡፡ ጅቦች ይሆናሉ ብሎ ስለፈራ አላበው፡፡

10

በድንገት በሰማዩ ላይ መብረቅ ታየ፡፡ ታሪክም በአካባቢው ያለውን ነገር ለማየት ቻለ፡፡

ቡቼ ቆሞ ከሁለት የሚጯጯሁና አስፈሪ ጅቦች እየተከላከለው ነበር፡፡

11

ቡቼ ታሪክን ከአውሬዎቹ አዳነው፡፡ ምን ዓይነት ጓደኛ ነው! ልጁ ቡቼን ይዞ ዛፉ ላይ ተመልሶ ወጣ፡፡

እንግዲህ እስኪነጋ አብረው ጠብቀው ወደ ቤት ሄደው የታሪክ አባት እንደሚያደርጋቸው ይሆናሉ፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
እረኛውና የልብ ጓደኛው
Author - Biniam Asfaw
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Isaac Okwir
Language - Amharic
Level - First paragraphs