

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የተራበ ቀበሮ ነበረ፡፡ ቀበሮው አንዲት የጫካ አይጥ ለመያዝ ሲሞክር የጫካ አይጧ ሮጣ አመለጠችው፡፡
ቀበሮውም እንደገና አንዲት ሽኮኮ አድኖ ለመያዝ ሲሞክር ሽኮኮዋም ሮጣ ዛፍ ላይ ወጣችና አመለጠችው፡፡ ከዚያም ቀበሮው አንዲት ትንሽ ወፍራም አይጥ አየ፡፡ "ለመብላት ጥሩ ትመስላለች" ሲል አሰበ፡፡ ትንሿ አይጥ ቀበሮውን አይታው ስለነበር በትልቅ ድንጋይ ሥር ሮጣ ወደ ጉድጓዷ ዘላ ገባች፡፡ ቀበሮውም "ይችን አይጥ ከጉድጓዷ ውስጥ ቆፍሬ ማውጣት አለብኝ" አለ፡፡
ከዚያም በትልቁ ድንጋይ ሥር ሮጦ ገባና መቆፈር ጀመረ፡፡ እጅግ በጣም ራቅ አድርጎ በጥልቀት ሲቆፍር ትልቁ ድንጋይ በቀበሮው መዳፍ ላይ ወደቀበት፣ መዳፉንም ጎትቶ ማውጣት አልቻለም፡፡ ቀበሮውም "ወይኔ እጄን ተያዝኩ እርዱኝ! እርዱኝ!" እያለ ጮኸ፡፡
ጥንቸልም ቀበሮው ሲጮህ ሰምታ እየሮጠች መጣች፡፡ "ምን ሆነህ ነው?" ብላ ጠየቀችው፡፡ "አንዲት አይጥ እያደንኩ ነበረ፣ይኸ ድንጋይ መዳፌ ላይ ወደቀብኝ፡፡ ውዷና አዛኟ ጥንቸል እባክሽን ርጅኝ!" አላት፡፡
ጥንቸሏም "እእእእ እኔ ብረዳህ በጣም ደስ ይለኛል፣ ነገር ግን ትንሽና ደካማ ነኝ፣ድንጋዩ ደግሞ በጣም ትልቅ ነው፤ ለኔ በጣም አስቸጋሪ ይሆንብኛል፡፡ ብረዳህ ምን ትሰጠኛለህ?" አለችው፡፡ ቀበሮውም "ኦኦኦኦ! የምትወጅውን ምግብ ለራትሽ አዘጋጅልሻለሁ፤በዓለም ላይ በጣም ጥሩ የሆነውን ምግብ ትበያለሽ" አላት፡፡ ጥንቸልም "እሺ! እረዳሃለሁ!" አለችው፡፡
ከዚያም ጥንቸሏ ድንጋዩን መግፋት ጀመረች፣ ነገርግን ልታንቀሳቅሰው አልቻለችም፡፡ እንደገና ደጋግማ ገፋችው፡፡ በመጨረሻም ድንጋዩ ከቀበሮው መዳፍ ላይ ተሽከርክሮ ወደቀ፡፡ ጥንቸልም በደስታ ሳቀች፡፡
"አሁን ሽልማቴን እፈልጋለሁ!" አለች፡፡ ቀበሮም "የምን ሽልማት?" ሲል ጠየቃት፡፡ "እኔ ምንም ሽልማት ልሰጥሽ አልችልም፤አሁን እኔ በጣም ርቦኛል፣ አንቺ ደግሞ ጥሩ ወፍራም ጥንቸል ነሽ፣ ስለዚህ ልበላሽ ነው" አላት፡፡ "ምን?" አለች ጥንቸል "ግን እረድቸሃለሁ፣እንደምትሸልመኝም ቃል ገብተህልኛል፤ አሁን እንዴት ትበላኛለህ?" አለችው፡፡ "እኔ ቀበሮ ነኝ፣ አንቺ ደግሞ ጥንቸል ነሽ፡፡ ቀበሮዎች ሁልጊዜ ጥንቸሎችን ይበላሉ፡፡ ከእኔ ጋር አትጨቃጨቂ" አላት፡፡ ጥንቸልም "ይኸ አግባብ አይደለም፡፡ ወደአባቶች መሄድና ምክራቸውን መጠየቅ አለብን" አለች፡፡.
"ስለዚህ ቀበሮና ጥንቸል ተያይዘው አባቶች ፍለጋ ሄዱ፡፡ በመጨረሻም አንድ ሽማግሌ አገኙ፡፡ ጥንቸልም "አባት! እባክዎትን ይርዱን" አለች፡፡ "ቀበሮ ሊበላኝ ፈለገ፣ እኔ ግን ህይወቱን አድኜዋለሁ፤ ትልቅ ድንጋይ መዳፉን ተጭኖት ማምለጥ አልቻለም ነበር፡፡ በጣም ጥሩ እራት ሊሰጠኝ ቃል ገባልኝ፣ እኔም ድንጋዩን ከመዳፉ ላይ ገፋሁለትና አዳንኩት፡፡ አሁን የገባውን ቃል ረሳው" አለች፡፡."
ሽማግሌውም "ይኸ ትክክል አይደለም፤ ቀበሮ! ውለታ ቢስ ነህ፣በል ጥንቸልን ተዋት፤ ትሂድ" አሉት፡፡ ቀበሮው ግን አፉን ከፍቶ ረጃጅም ጥርሶቹን ለሽማግሌው አሳያቸው፡፡ ከዚያም "አይ! አለቃትም፣አባባ ሊያስቆሙኝ አይሞክሩ፣ ያለዚያ እርስዎንም እበላዎታለሁ" አላቸው፡፡ ሽማግሌውም ፍርሃት ተሰማቸው፡፡
"እባክህ እኔን አትብላኝ፣ ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል፤ ምናልባትም አንተ ትክክል ልትሆን ትችላለህ፤ ድንጋዩን ሳላይ መወሰን አልችልም፣ በትክክል የተፈጠረው ነገር ምንድነው?" አሉ፡፡.
ቀበሮዉም "ኦኦኦ! ያ በጣም ቀላል ነው፤ ይምጡ ላሳይዎት" አለ፡፡ ሽማግሌውም ከቀበሮዉና ከጥንቸሏ ጋር ወደ ድንጋዩ ሄዱ፡፡ "ቀበሮ! አንተ ምን እያደረክ ነበር?" አሉት፡፡
"እያደንኳት የነበረችው አይጥ ሮጣ ወደጉድጓዷ ስለገባች እሷን ለማውጣት ስቆፍር ድንጋዩ መዳፌ ላይ ወደቀብኝ" ሽማግሌዉም "የትኛው ድንጋይ?" አሉ፡፡ "ይኸ" አለ ቀበሮ፡፡ "እና አንተ የት ነበርክ?" አሉ ሽማግሌው፡፡ ቀበሮዉም "እዚህ ነበርኩ" አለና መሬቱ ላይ ተጋደመ፡፡.
ሽማግሌውም ጥንቸልን ተመለከቷት፡፡ "አንቺ ትንሽ ጥንቸል ነሽ፣ ትንሽና ደካማ! እኔ አንቺ ይኸን ትልቅ ድንጋይ ማንቀሳቀስ ትችያለሽ ብዬ አላምንም" አሏት፡፡ ጥንቸልም "ግን አድርጌዋለሁ! አድርጌዋለሁ!" እያለች ጮኸች፡፡ ሽማግሌዎም "እስቲ አሳይኝ" አሉ፡፡
ጥንቸልም ድንጋዩን ደጋግማ ስትገፋው በቀበሮው መዳፍ ላይ ወደቀ፡፡ ሽማግሌዉም "ቀበሮን ያገኘሽው እንደዚህ ነው?" አሏት፡፡ ጥንቸልም በአዎንታ ራሷን ነቀነቀች፡፡
"ሽማግሌው ቀበሮን በተራው "ጥንቸል ያገኘችህ እንደዚህ ነው?" ሲሉ ጠየቁት፡፡ ቀበሮም በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ፡፡ "ጥሩ!" አሉ ሽማግሌው "ስለዚህ አሁን ሁሉም ነገር ተስተካክሏል፤ በአግባቡ ሆኗል፡፡ ጥንቸል! ሩጪና ወደ ቤትሽ ሂጂ፣እኔም ወደቤቴ እሄዳለሁ" አሉ፡፡."
ስለዚህ ሽማግሌውና ጥንቸሏ ዉለታ ቢሱን ቀበሮ ከድንጋዩ ሥር ትተዉት ሄዱ፡፡

