ታዳጊው አበራ
Gaspah Emukuru Juma
Wiehan de Jager

ከዘመናት በፊት አበራ የተባለ ወላጅ - አጥ ህፃን ነበር፡፡ አበራ ገና የስድስት ወር ህፃን እያለ ነበር ወላጆቹ በወሮበሎች የተገደሉት፡፡ የሰፈሩ ሰዎች በሃዘን ላይ ሆነው አበራ ምን እንደሚሆን ያስቡ ነበር።

1

የሰፈሩ ሰዎች የህፃኑን ወላጆች ከቀበሩ በኋላ የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ ጥበቡ ስብሰባ ጠሩ፡፡ አቶ ጥበቡ ፀጉረ-ረዥም ሲሆኑ በአካባቢው ሰዎች ዘንድም እጅግ የሚከበሩና የሚፈሩ ነበሩ፡፡ አቶ ጥበቡ ድሮ ድሮ ዛፎች ሳይቆረጡና ቤቶች ሳይገነቡ በጫካ ውስጥ ይኖሩ ነበር  ተብሎ ይታመናል።

2

አቶ ጥበቡ ስብሰባ የጠሩት ስለ ህፃኑ ለመወያየት ስለነበር አንድ የመንደሩ ከበርቴ የሆነ ላቀው የተባለ ሰው አበራን ለማሳደግ ይወስደዋል። አቶ ላቀው ብዙ ሴትና ወንድ ልጆች ነበሩት። ሴቶቹ እናታቸውን በቤት ውስጥ ስራ ሲያግዙ ወንዶቹ ደግሞ የአባታቸውን ከብቶች እንዲጠብቁ ይላኩ ነበር።

3

አበራም በቤተሰቡ ውስጥ አደገ፤ በጣም ደስተኛም ነበር። በጣም ተወዳጅና ሁሉንም የሚወድ ነበር። በሜዳ ላይ ሆኖ ከብቶቹን መጠበቅ በጣም ያዝናናው ነበር።

4

አበራ አንዷን ላም በጣም ይወዳት ስለነበር 'ቦራ' ብሎ ስም አወጣላት፡፡ ቦራ ከከብቶቹ ሁሉ በጣም ያገለገለች ነበረች። በዚህም ምክንያት ባለቤትየው ከፍተኛ ዋጋ ይሰጧት ነበር።

5

አንድ ቀን እነአበራ ከብት በመጠበቅ ላይ እያሉ ሃይለኛ ዝናብ ይጥል ጀመር፡፡ እነርሱም ዝናቡ እስኪያባራ ብለው ዛፍ ሥር ቁጭ አሉ፡፡ ነገር ግን ለዓይን አስኪይዝ ድረስ ዝናቡ አላባራ አለ። ቆይቶ ዝናቡ አባራ፤ ነገር ግን ከብቶቻቸውን  ወደ ቤት ለመውሰድ ሲፈልጓቸው የሉም፡፡

6

ከብቶቹን ሳናገኝ ወደ ቤት ከሄድን አባታችን አያስገባንም አሉና ሁለቱ  ልጆች ወደ አጎታቸው ቤት ሄዱ፤ ሁለቱ ደግሞ ወደ አክስታቸው ቤት ሄዱ፡፡ ነገር ግን አበራ አጎትም ሆነ አክስት ስለሌለውና መሄጃ ስላጣ ከብቶቹን እስኪያገኛቸው ድረስ ለመፈለግ ወሰነ፡፡

7

አበራ የሚወደውን የላሟን  ዘፈን እየዘፈነ ከብቶቹን በሚያውቀው ሥፍራ ሁሉ ፈለጋቸው። ''እምቧ በይ ላሜ ቦራ! እምቧ በይ እምቧ! ላሜ ቦራ እማቧ በይ! ---'' እያለ ፍለጋውን ቀጠለ፡፡

8

አበራም ዘፈኑን እየዘፈነ ሌሊቱን በሙሉ ፍለጋውን ቀጠለ። የላም እበት ላይ እግሩ አረፈ፤ እበቱ ግን ቀዝቃዛ ነበር። የላም ሽንትም ላይ እግሩ አረፈ፤  ሽንቱ ግን ቀዝቃዛ ነበር። አበራ ግን ተስፋ አልቆረጠም።

9

ሌሊቱን በሙሉ ሲፈልግ ከቆየ በኋላ ሊነጋ ሲል አንዲት ትንሽዬ መንደር አገኘ፡፡ ከብቶቹንም በመንደሩ አስተዳዳሪ ቤት አገኛቸው፡፡ ለመንደሩ ሊቀመንበር ከብቶቹን እንዲሰጡት ተማፀነ፤ ነገር ግን ሊቀመንበሩ ''አይሆንም አልሠጥም!'' አሉት፡፡

10

በዚህ ተስፋ የቆረጠው አበራ ዘፈኑን እየዘፈነ ወደቤቱ መመለስ ጀመረ፡፡ ''እምቧ በይ ላሜ ቦራ! እምቧ በይ እምቧ በይ! ላሜ ቦራ እምቧ በይ!'' ሲል ቦራ ተከተለችው፡፡ ከዚያም ሁሉም ከብቶች በረቱን ጥሰው ወጡና አበራን ተከትለው ሄዱ፡፡ እሱም ወደ ቤት መራቸው።

11

አበራ ቤቱ ሲደርስ የሠፈሩ ሰው እንዳለ ወጥቶ ስሙን እየጠራና እያወደሰ ተቀበለው፡፡ አቶ ላቀው በጣም አመስግነው ቀይ የትምህርት ቤት ቦርሳ ገዝተው ሸለሙት፡፡ እናም ትምህርት እንዲማር አደረጉት፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ታዳጊው አበራ
Author - Gaspah Emukuru Juma
Translation - ከድር ኢብራሂም, ፋሲካ ምንዳ, መዘምር ግርማ
Illustration - Wiehan de Jager
Language - Amharic
Level - First paragraphs