

በአንድ ውብ ቤተ መንግስት ዉስጥ የሚኖር “ልዑል አማኑኤል” የሚባል ደግና ንቁ ልጅ ነበር። ሌሎቹ የቤተመንግሥት ልጆች በሰይፍ ጨዋታና በፈረስ ጉግስ ሲሽቀዳደሙ ፣ ልዑል አማኑኤል ግን በእጆቹ ቀለማትና ብሩሾችን ይዞ መሥራት ይወድ ነበር።
አንድ ቀን አባቱ ልዑል አማኑኤልን ጠርተው “ልጄ አማኑኤል! ንጉሥ የሚሆንው ሰው ኃይለኛና ጠንካራ መሆን አለበት። አንተ ግን ቀኑን ሙሉ ሥዕል ስትስል ትውላለህ፤ ይህ ለሀገር ምን ይጠቅማል?” አሉት። ልዑል አማኑኤልም ፈገግ ብሎ “አባቴ፣ ሥዕል ከሰይፍ በላይ የሰዎችን ልብ የመማረክና ፍቅርን የማስተማር ኃይል አለው” አላቸው።
በዚያዉ ሳምንት በጎረቤት ሀገራት መንግሥት መካከል ትልቅ አለመግባባት ተፈጠረ። የጎረቤቱ ሀገር ንጉሡም በቁጣ ተሞልቶ ወደ ጦርነት ለመግባት ሰራዊቱን አዘጋጀ። ንጉሡ አባቱ በጭንቅ ላይ እያሉ፣ ልዑል አማኑኤል አንድ ድንቅ ሃሳብ አመጣ።
ልዑል አማኑኤል ሌሊቱን ሙሉ ሳይተኛ በትልቅ ጨርቅ ላይ ውብ ሥዕል ሣለ። ሥዕሉም የሁለቱ ሀገራት ህፃናት አብረው ሲጫወቱ፣ እናቶች በደስታ ቡና ሲያፈሉ፣ እና አባቶች በእርሻ ላይ አብረው ሲሰሩ የሚያሳይ ነበር። በሥዕሉ መሃል ደግሞ ሁለቱ ነገሥታት እጅ ለእጅ ተያይዘው ይታዩ ነበር።
በማግስቱ ጦርነቱ ሊጀመር ሲል፣ ልዑል አማኑኤል ሥዕሉን ይዞ በመስኩ መሃል ቆመ። የጎረቤቱ ንጉሥና ሰራዊቱ ሊያጠቁ ሲመጡ ሥዕሉን ተመለከቱ። ሥዕሉ ላይ ያለው የሰላምና የፍቅር ምስል የንጉሡን ልብ በጽኑ ነካው፤ የጦርነትን አስከፊነትና የሰላምን ውበት ግልጽ አድርጎ አሳያቸው።
የጎረቤቱ ንጉሥ ሰይፉን ወደ ታች አወረደና “ይህ ልጅ በቃላትና በጦር ሊገለጽ የማይችል ትልቅ የሰላም መልእክት አሳየን!” አለ። በዚያው ዕለት ሁለቱ ነገሥታት ታረቁ።
ንጉሡ አባቱም ልጃቸውን አቅፈው “ልጄ አማኑኤል! እውነተኛ ጥበብና ደግነት ከማንኛውም ጦር መሳሪያ በላይ ሀገርን እንደሚያድን ዛሬ አስተማርከኝ” አሉት።ትልቅ ድግስም ተደገሰ።
ከዚያች ቀን ጀምሮ ልዑል አማኑኤል “ሠዓሊው ልዑል” በመባል በግዛታቸዉ ዉስጥ ታወቀ፤ በፍቅርና በጥበቡም ሀገሩን በሰላም እንዲያስተዳድር አባቱ ግዛቱን ሰጠዉ።
ከዚህ ተረት ምን እንማራለን?
የእያንዳንዱ ሰው ስጦታ ልዩ እንደሆነ እና ሁሉም ሰው ጉልበተኛ መሆን የለበትም፤ ጥበብ፣ እውቀትና ደግነት ትልቅ ኃይል እንዳላቸዉ
ሰላም ከጦርነት እንደሚበልጥ ችግሮችን በጠብ ሳይሆን በፍቅር፣ በውይይትና በጥበብ መፍታት መልካም እንደሆነ ያስተምረናል።

