

ተፈጥሮ በከበባት ውብ መንደር ውስጥ “ፍሬ” የምትባል በጣም ብልህና ደግ ልጅ ከቤተሰቧ ጋር ትኖር ነበር። ፍሬ አባቷን በጣም ትወደዋለች፤ አባቷ ደግሞ ዘወትር ጠዋት ማልዶ ተነስቶ ለቤተሰቡ ብሎ ወደ እርሻ በመሄድ ቀኑን ሙሉ በጥንካሬ ይሰራል።
አንድ ቀን ፍሬ ከትምህርት ቤት ስትመለስ አባቷ ከስራ ተመልሶ በጣም ደክሞት የዛፍ ጥላ ስር አርፎ ተመለከተች። ፍሬ አባቷ ለነሱ ብሎ የሚያደርገውን ድካም አሰበችና ልቧ በትልቅ ፍቅርና በትልቅ ምስጋና ተሞላ።
ወዲያውኑ ወደ ክፍሏ ገብታ ባለቀለም እርሳሶቿንና ደብተሯን አወጣችና በጥንቃቄ በመቅረፅም፣ በአበቦችና በወፎች ስዕል አሸብርቃ ለአባቷ አንድ ውብ ደብዳቤ መጻፍ ጀመረች።
ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፦
“ውድ አባቴ...
በየቀኑ ጠዋት ማልደህ ተነስተህ ስትሰራ አይሃለሁ። እኛን ለማሳደግ፣ ጥሩ ምግብ እንድንበላና ትምህርታችንን እንድንማር የምታደርገው ጥረት ሁሉ በጣም ደስ ይለኛል።የምወድህ አባቴ! ላንተ ያለኝን ፍቅር በቃላት መግለጽ ባልችልም፣ ሁልጊዜ በልቤ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለህ።
ከአንተ የተማርኩትን ታታሪነት፣ እውነተኛነትና ደግነት ይዤ አድጋለሁ። እኔም በትምህርቴ ጠንክሬ በመማርና ጎበዝ ልጅ በመሆን ሁልጊዜ ደስ እያሰኘሁህ አኮራሃለሁ! ስለ ሁሉም ነገር በጣም አመሰግናለሁ፤ በጣም እወድሃለሁ አባቴ!” ከልጅህ ፍሬ ብላ ደብዳቤዋን ጨረሰች።
ፍሬ ደብዳቤዋን ፅፋ ስትጨርስ፣ በፍቅር አጥፋ አባቷ የተቀመጠበት ቦታ ሄደችና በእጆቹ ሰጠችዉ።
አባቷም ደብዳቤውን ገልጦ ሲያነበው በደስታ ፊቱ አበራ፤ ድካሙም በሙሉ ብን ብሎ ጠፋ! "ፍሬ ልጄ ነይ!" ብሎ አቅፎ ሳማትና “ፍርዬ ልጄ! ላንቺ ስል መስራትና አንቺን ደስተኛ ማድረግ ለእኔ ትልቁ እረፍቴ ነው” አላትና አይኖቹ በእንባ ተሞልቶ አቅፎ ሳማት።
ከዚያች ቀን ጀምሮ ፍሬና አባቷ የበለጠ ተቀራረቡ፤ ፍሬም አባቷን የምታከብርና የምታስደስት ጎበዝ ልጅ ሆነች።
ከዚህ ተረት ምን እንማራለን
ወላጆችን ማመስገንና ማክበር:- ወላጆቻችን ለእኛ ብለው የሚያደርጉትን ድካም መረዳትና በትንሹም ቢሆን ምስጋናችንን መግለጽ እንደሚያስደስታቸው፤ ፍቅርን መግለጽ፦ ወላጆቻችንን ወይም የምንወዳቸውን ሰዎች ምን ያህል እንደምንወዳቸው በስዕል፣ በደብዳቤ ወይም በቃል መግለጽ መልካም እንደሆነ ከዚህ ተረት እንማራለን።

