

ዛሬ ለእኔ ልዩ ቀን ነዉ! እናቴ የገዛችልኝን አዲስ ጫማ ተጫምቼ፣እግሬን እያየሁ በደስታ ከእናቴ ጋር ወደ ገበያ ሄድን።ገበያው ግርግር የበዛበት ነበር፤ እኔ ግን ወደ አንዱ ጥግ ስመለከት ዓይኖቼ በአንድ ቦታ ላይ ተተከሉ። በየቦታው በትልልቅ ጆንያዎች የተሞሉ በቀለማት ያሸበረቁ ነገሮች ተደርድረዋል! አንዳንዶቹ ደማቅ ቀይ፣ ሌሎቹ ቢጫ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ቡናማና ጥቁር ነበሩ።
ጉጉቴን መግታት አቅቶኝ የእናቴን እጅን እየጎተትኩ፣ "እማዬ...በእነዚህ ትልልቅ ጆንያዎች ውስጥ ምንድነዉ ያለዉ ?" ብዬ ጠየቅኳት።እናቴም በእጇ እየነካ መቁጠር ጀመረች፦ "ጥቁር አዝሙድ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ በሶብላ፣ ዝንጅብል፣ ጦስኝ፣ ኮረሪማ…" እያለች ነገረችኝ።
እኔም እያንዳንዱን እንግዳ ስም በጭንቅላቴ ለመያዝ እየሞከርኩ፣ አፌን ከፍቼ "እማዬ! እነዚህ ሁሉ ይበላሉ እንዴ? ምግብ ናቸው?" አልኳት።እናቴ ፈገግ ብላ፣ "አይ ልጄ፣ እነዚህ ቅመማ ቅመሞች ይባላሉ" አለችኝ። "ለምግብ ልዩ መዓዛና ጣዕምን ይሰጣሉ፤ ወጡንም ሆነ ሌላውን ምግብ የሚያጣፍጡት እነዚህ ቅመሞች ናቸው!" የገዛናቸውን ቅመሞች ጥቅም ቤት ስንደርስ እናቴን ለመጠየቅ አሰብኩ።
ነገር ግን ያልገዛናቸውን ቅመሞች ምስጢር አሁኑኑ ለማወቅ ቸኮልኩ! እጄን ዘርግቼ አንዱን እየጠቆምኩ "እማ፣ የዚህኛው ቅመም ጥቅም ምንድን ነው?" አልኳት።
"ቅርንፉድ ይባላል ልጄ" አለችኝ፤ ከዚያም ጥቂት ቅርንፉድ በእጇ ዘግና ወደአፍንጫዬ አቀረበችው። መዓዛው በአፍንጫዬ ሳሸተዉ ልቤን ደስ አለው! እናቴም በመቀጠል "ቅርንፉድ ሻይን ያጣፍጣል፣ለበርበሬና ለሽሮም ልዩ መዓዛ ይሰጣል።"
ጣዕሙን ለመቅመስ ቸኩዬ፣ "እባክሽን እማዬ! ከዚህ ትንሽ ገዝተን ቤት ስንደርስ ጣፋጭ ሻይ አፍልተን እንጠጣ!" ብዬ ለመንኳት።ከዚያም እኔና እናቴ እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ በርበሬ ተራ አመራን። በርበሬ ተራ ስንደርስ የበርበሬው ደማቅ ቀይ ቀለሙና ቅመምነቱ አየሩን ሞልቶታል። እናቴ የምትፈልገውን የበርበሬ ዓይነት መርጣ ዋጋዋን ጠየቀች።
ወዲያውኑ ግን እጇን ጭንቅላቷ ላይ አድርጋ "ጉድ! ጉድ!" አለች። ደንግጬ "እማ! ምን ሆንሽ? ምን አጋጠመሽ?" አልኳት።
እናቴም ወደ ሻጩ ዞራ "ምነው አባቴ... ዋጋው እንዲህ ሰማይ ወጣ?" አለች በግርምት።
ከቤት ስንወጣ አምስት ኪሎ በርበሬ ለመግዛት አቅደን የነበረ ቢሆንም፣ የዋጋው ነገር አልሆንልን ስላለን ሁለት ኪሎ ብቻ ገዝተን፣
እኔ አዲሱን ጫማዬን እየተመለከትኩ፣ እናቴ ደግሞ ስለ ዋጋው እያሰበች ወደ ቤታችን ተመለስን።

