ተኩላው፣ አይጧ እና ዶሮዋ
ይስሀቅ አስጨናቂ
ይስሀቅ አስጨናቂ

በአንድ ወቅት በአንድ ጫካ ውስጥ አንድ ተኩላና አንዲት አይጥ ይኖሩ ነበር።ከዕለታት አንድ ቀን በመንገድ ላይ ተገናኙ።አይጧም፦“እንዴት አደርክ፣ ተኩላ?” አለችው።
ተኩላውም፦“እንዴት ነሽ፣ አይጥ? ወዴት እየሄድሽ ነው?” ብሎ ጠየቃት።

1

አይጧም፦“እኔ ወደ ጓደኛዬ ቤት እየሄድኩ ነው” አለችው።ተኩላውም፦“እኔማ በጣም ርቦኛል፤ ምግብ ፍለጋ እየሄድኩ ነው” አላት።አይጧም በደስታ፦“እንግዲያስ ለምን አብረን አንሄድም? ጓደኛዬ ዶሮ ለምሳ ጋብዛኛለች” አለችው።

2

ተኩላው ይህን ሲሰማ በጣም ተደሰተ። የአይጧንም ሀሳብ ተቀብሎ አብረው ወደ ዶሮዋ ቤት መሄድ ጀመሩ።ብዙ ከተጓዙ በኋላ የዶሮዋ ቤት ደረሱ።አይጧም፦“ይህች ጓደኛዬ ዶሮ ትባላለች” ብላ አስተዋወቀችው።

3

ዶሮዋም በደስታ ተቀብላቸው። ከዚያም ሰላምታ ካቀረበችላቸው በኋላ፦“እንግዲህ ምሳ እንብላ!” አለቻቸው።ሦስቱም ተቀምጠው ምሳቸውን መብላት ጀመሩ።ነገር ግን ተኩላው እጅግ ስለተራበ ከምሳው በኋላም አልጠገበም።

4

ተኩላው ለጥቂት ጊዜ አሰበና አንድ አታላይ ሀሳብ መጣለት።አይጧንም፦“አይጥ ሆይ፣ እባክሽ ከቤት ውጭ ያስቀመጥኩትን እቃ አምጪልኝ” አላት።አይጧም ምንም ሳትጠራጠር እቃውን ለማምጣት ወደ ውጭ ወጣች።

5

ተኩላውም አይጧ ከቤት እንደወጣች ጠብቆ ዶሮዋን ያዘና በላት።ከዚያ በኋላ አይጧ እቃውን ይዛ ተመለሰች።“ይኸው ያልከኝን እቃ አመጣሁልህ” አለችው።ነገር ግን ወደ ቤት ውስጥ ስትመለከት ጓደኛዋ ዶሮ አልነበረችም።አይጧም በጭንቀት፦“ተኩላ ሆይ፣ ጓደኛዬ ዶሮ የት ሄደች?” ብላ ጠየቀችው።

6

ተኩላውም እውነቱን እንዳታውቅ ፈልጎ፦“ወደ ገበያ ሄዳለች። ትመጣለች፤ እስክትመጣ ቁጭ ብለን እንጠብቃት” አላት።አይጧም ጓደኛዋ ትመጣለች ብላ በማሰብ ከተኩላው ጋር ቁጭ ብላ መጠበቅ ጀመረች።

7

ነገር ግን አታላዩ ተኩላ የዶሮዋን እጣ ለአይጧም ሊደግም አስቦ ነበር።ከኋላዋ በድንገት ዘሎ አይጧን ያዛት።አይጧም የተኩላውን አታላይነት ሳታውቅ ስለነበር ለማምለጥ አልቻለችም። ተኩላውም አይጧን እንደ ዶሮዋ በላት።

8
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ተኩላው፣ አይጧ እና ዶሮዋ
Author - ይስሀቅ አስጨናቂ
Illustration - ይስሀቅ አስጨናቂ, ረድኤት ሲሳይ
Language - Amharic
Level - First paragraphs