

በአንድ አነስተኛ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ገበሬ ነበር ።ገበሬውም ላም፣በሬ እና አህያ ነበረው።ገበሬውም እንስሳቱን በጣም ይወዳቸው ነበር።አብረው እንዲበሉ የተሰጣቸውንም ሣር ክፉው በሬ ብቻውን ይበላ ነበር።
እነርሱም በጣም ይናደዱበት ነበር። አላስበላ ስለሚላቸው ወደ ውጪ እየወጡ ይበሉ ነበር።ከዕለታት አንድ ቀን እንደተለመደው ሳር ፍለጋ ከቤታቸው ሲወጡ በመንገዳቸው ላይ ለምለም ሳር እና ውሀ አገኙ ።አስኪጠግቡ ድረስም በደንብ በሉ ጠጡ።
ወደ ቤታቸውም እንደተመለሱ ለበሬዉ ስላገኙት ለምለም ሣርንና ውሃ ነገሩት።በሬውም በጣም ጎመጀ ፡፡መሽቶም ወደ በረታቸው ሄደው ተኙ።በሬው ግን ለምለሙን ሳር እና ውሃ እያሰበ መተኛት አልቻለም። ሳሩን የሚበላበትን መንገድ ማሰብ ጀመረ።በድንገት አንድ ሀሳብ ብልጭ አለለት።ሃሳቡም እነሱ የሚበሉትን ለምለም ሳር እና ውሃ ወዳለበት ቦታ ተከትሎ ሄዶ መብላት ነበር።
በነጋታው ጠዋትም ገበሬው ለሁሉም የሚሆን ሳር ሰጥቷቸው ሄደ ።እንደ ሁልጊዜውም ሁሉንም ሳርና ውሃ በልቶ ጨረሰው።እነሱም ትተውት ሄዱ።ተከትሏቸውም ሄደ።እነርሱም አዩትና "አንተ ክፉ አትከተለን!" አሉት።"እኔም ለምለሙን ሳር እና ውሃ መብላት እና መጠጣት እፈልጋለሁ" አላቸው።እነሱም" አንተ ባለቤታችን የሚሰጠንን ሣር እና ውሃ እየበላህ አይደል?" አሉት።
በሬውም እያለቀሰ "እባካችሁ ይቅርታ አድርጉልኝ "አለ።እነሱም" እሺ ይቅርታህን ተቀብለናል "አሉት። እሱም ይቅርታውን ስለተቀበሉት አመሰግናቸው።ከዛም አብረው ሄደው ጣፋጩን ለምለም ሣር እና ውሃ እስኪጠግቡ ድረስ በደንብ በሉ ጠጡ።
ወደ ቤታቸውም እንደተመለሱ ገበሬው ያስቀመጠላቸውን ለምለም ሳር እና ውሃ በሉ ጠጡ።በሬው ከጥፋቱ ተምሮ ብቻውን መብላቱን ትቶ ተካፍለው መብላት ጀመሩ።ከዛን ቀን ጀምሮ በሰላም በፍቅር ሳይጣሉ እየተካፈሉ መብላት ጀመሩ።

