

በድሮ ዘመን ጫካ ውስጥ የሚኖር አንበሳ ነበር።አንበሳውም ራሱን በጫካ ውስጥ ጉልበተኛ አድርጎ ይቆጠር ነበር።አንበሳም ሁልጊዜ ያገኘውን የዱር እንስሳት ሁሉ ያስፈራራ ነበር።
በዚህም ምክንያት አንበሳውን ሲያዩት በፍራት ይሮጡ ነበር ከእለታት አንድ ቀን አንበሳው ውሃ ጠምቶ ሊጠጣ ወደ ወንዝ ሔደ።ጠጥቶ ሲጨርስ ከወንዙ ዳር ቁጭ ብሎ" እኔን አንበሶን በጉልበት ማንም አይበልጠኝም"ብሎ ሶስት ጊዜ አገሳ።
በዚህም ጊዜ ወንዞች ውስጥ የነበረው አዞ አንበሳውን ሰምቶት ተናደደ።አዞውም አንበሳውን እንዲህ አለው" አያ አንበሶ እኔ በዚህ ጫካ ውስጥ ጉልበተኛ ነኝ ብለህ የምታምን ከሆነ ተሳስተሀል ምክንያቱም ሌሎች ብዙ የሚበልጡ ጉልበተኞች አሉ"አለው።
አንበሳም በንዴት" እንዴት ደፋር ነህ እኔ አንተን ስልቅጥቅጥ አድርጌ መብላት እንደምችል አታውቅም" አለው።አዞውም በዚህ መልስ በጣም ተናዶ" ንጉስ አንበሶ ጫካውን በጥንቃቄ የማትጠብቅ ከሆነ የጫካው እንስሳቶች ተባብርን ልናጠፋህ እንችላለን" አለ።
ከዚያም አያ አንበሶ በንዴት አገሳ።"ደሞ ለናንተ ማን ይጠነቀቃል ሁላችሁንም ስልቅጥቅጥ አርጌ መብላት እችላለሁ" ብሎ አንበሳው አዞውን ሊበላው ሲል ዉሀ ውስጥ ዘሎ ገባ። ወንዙም በጣም ጥልቅ ስለነበር መውጣት ተቸገረ።
ከዚህም በኋላ አንበሳው ረዳት ለማግኘት መጮህ ጀመረ" እባካችሁ መውጣት አልቻልኩም ድረሱልኝ" እያለ በኃይል መጮህ ጀመረ።ይህ ሲሆን ይመለከቱት የነበሩት የጫካው እንስሳት አዝነው ከውሃ ውስጥ አውጡት።
አንበሳውም እስከ ዛሬ ባደረገባቸው ድርጊት አዝኖ ይቅርታ ጠየቃቸው ።እንስሳቶቹም ይቅርታ አደረጉለት። ከዚያን ቀን ጀምሮ በጫካ ውስጥ ሰላም ፣ፍቅር እና ደስታም ሆነ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንስሳቶቹን ማስፈራራት ተወ።
ሁሉም እንስሳት በኩል መከባበር ጀመሩ። አንበሳውም ጫካውን በስርዓት ማስተዳደር ጀመረ ።አንበሳውም የደረሰበት ነገር ከባድ እንደሆነ ተረዳ እንስሳቶቹም ባይኖሩ ኖሮ እንደሚሞት አሰበ እንስሳቶቹንም አመሰገነ ።አንበሳውም ተፀፅቶ ከክፉ ተግባሩ ተቆጠበ።እንስሳቶቹም በሰላም መኖር ጀመሩ።

