

በአንዲት ትንሽዬ መንደር ውስጥ የምትኖር አንድ አስቸጋሪ ህፃን ነበረች።
ይህች ህፃን የምትኖረው ከእናቷ እና ከእህቷ ጋር ነው።እህቷ ታላቋ ነች።
እናቷ የምትሰራው ዶሮ ማርባትና ከብቶችን ማደለብ ነው።ልክ እንደ አርብቶ አደሮች ማለት ነው።እናቷ ለስራዋ ታታሪ ነበረች።ጎንበስ ቀና ስትል ቀኑን ሙሉ ስትደክም ውላ ማታ ላይ ነው እረፍት የምታደርገው። የመጀመሪያ ልጇ እድሜዋ ከሁለተኛ ልጇ በ5 አመት ትበልጣለች። የመጀመሪያ ልጇ 7 አመቷ ሲሆን ሁለተኛዋ ደግሞ 2 አመቷ ነው።
ይህች ህፃን በጣም አስቸጋሪ ነበረች።ምግብ ቀርቦላት በልታ ከጨረሰች በኋላ የበላችበት ሰሀን በእግሯ ወይም እላዩ ላይ ቁጭ ብላ መስበር ያስደስታታል።
ይህንን የሚያውቁት እናት እና እህቷ በልታ እስከምትጨርስ ድረስ ቁጭ ብለው ይጠብቋታል።
አንድ ቀን እናቷ ስራ በጣም በዝቶባት እቃ አላጠበችም ነበር።ብፌ ውስጥ በጣም የሚያምር የሰው ስጦታ ሰሀን ነበራት።እሱን ሰሀን አውጥታ ምግብ አቀረበችላት።እናቷ ሰሀኑ በጣም ወፍራም ስለነበር ትሰብረዋለች ብላ አላሰበችም ነበር።ስራ ስራዋን ስትል ቆየች።
ልጅቷ በልታ ጨርሳ ሰሀኑ ላይ ቆማ ሰብራዋለች።እናቷ ስትመጣ ሰሀኑ ተሰብሮ አየች።በጣም ተናድዳ መታቻት። ልጅቷም ምርር ብላ አለቀሰች።
በሁለተኛው ቀን ምሳ ሰዓት ላይ እንደተለመደው ምግብ ቀረበላት።እናቷ ስለመታቻት ከዚህ በኋላ ትሰብራለች ብላ አላሰበችም።ልጅቷን ችላ ብላ ስራዋን ተያያዘችው።ነገር ግን ልጅቷ ዛሬ ደግሞ ሰሀኑን ቁጭ ብላ ሰብራዋለች።
እናቷ መጣች አይታ በጣም ተናደደች።ነገር ግን አሁን የልጅቷ ሳይሆን የእናትየዋ ነው ጥፋቱ ምክንያቱም ልማዷን እያወቀች ጥላት መሄድ አልነበረባትም።ንዴቷን ዋጥ አድርጋ ይዛ ምን ማድረግ እንዳለባት ማሰብ ጀመረች።አንድ ሀሳብ መጣላት የብረት እና የፕላስቲክ ሰሀን መግዛት እንዳለባት አሰበች።
በነጋታው ገበያ ሄዳ የብረት እና የኘላስቲክ ሰሀን ገዝታ መጣች።ከዛ በኋላ በኘላስቲክ ሰሀን ምግብ ቀረበላት።
ልጅቷ በልታ እንደጨረሰች እንደለመደችው ለመስበር ትጣጣር ጀመር።በእግሯ ብትረግጠው ብትቀመጥበት አልሰበር አላት አለቀሰች።
እናቷ መጥታ አባበለቻት "ለካ ስህተት ሲደገም ውሳኔ ይሆናል" አለች ለራሷ።ከዛ ጊዜ በኋላ እናትየዋ ሰሀን ተሰብሮባት አያውቅም።አሁን እናትየዋ "እፎይ" ብላለች።ልጅቷም ይሄ መጥፎ ልማዷን እርግፍ አድርጋ ትታለች።

