

ቅድመ - ንባብ ጥያቄዎች
ምን ምን ጨዋታዎች ትችላላችሁ?
ከማን ጋር ነው የምትጫወቱት?
ጓደኝነት ማለት ምን ማለት ነው?
በሽፋን ሥዕሉ ላይ የምታዩአቸው የቤት እንስሳት ምን ምን ናቸው?
ቡችላ፣ ውርዬና ጫጩት የቤት እንስሳት ናቸው፡፡
አንድ ቀን ሦስቱም መንገድ ላይ ተገናኝተው እንተዋወቅ! እንተዋወቅ! ተባባሉ፡፡
እኔ ቡችላ ነኝ፡፡ እናትና አባቴ ውሾች ናቸው፡፡
እኔ ውርዬ ነኝ፡፡ እናትና አባቴ ድመቶች ናቸው፡፡
እኔ ደግሞ ጫጩት እባላለሁ፡፡ እናትና አባቴ ዶሮዎች ናቸው፡፡
በጣም ስለተግባቡ አብረን እንድንበላ፤ ምግብ እናሰባስብ ተባባሉ፡፡
ቡችላ ‹‹እኔ አጥንት ሰብስቤያለሁ›› አለ::
ውርዬ በበኩሏ ‹‹እኔም ወተት አቅርቤአለሁ:: አንቺስ ጫጩት?›› አለቻት
ጫጩትም ‹‹እኔም ጥራጥሬ አምጥቻለሁ›› አለች፡፡
ሦስቱም ያሰባሰቡትን ምግብ ተመገቡ:: ቀጥለውም ‹‹ምግባችንን በልተናል፤ አሁን ደግሞ የገመድ ዝላይ እንጫወት›› ብለው ተስማሙ፡፡
ቡችላ ‹‹ገመድ መዝለል እችላለሁ›› አለ::
ውርዬም በተራዋ ዘለለች፡፡
ጫጩት የኔ ተራ ነው ብላ ዘለለች፡፡
ጫጩት ‹‹ሦስታችንም አብረን እንዝለል›› አለች፡፡ ውርዬ ‹‹ጥሩ ነው፤ ግን ገመድ ማን ይይዛል?›› የሚል ሃሳብ አመጣች፡፡ ቡችላም ‹‹ገመዱን በነዚህ ዛፎች እንሠር›› አለ:: ሦስቱም አብረው ሲዘሉ ጫጩት ለመቅደም ስትሞክር ወደቀች፡፡
ጫጩትም ገመድ ስትዘል በመውደቅዋ ‹‹ፂው! ፂው! ፂው!" ብላ አለቀሰች፡፡
ቡችላና ውርዬ ‹‹አይዞሽ ጫጩት አታልቂሺ" ብለው እቅፍ አድርገው በመሳም አበረታቷት፡፡
ጫጩትም ጓደኞቿ እቅፍ አድርገው በመሳም ስላጽናኗት በጣም ተደሰተች፡፡
ድህረ- ንባብ ጥያቄዎች
ጫጩት ለምን ተደሰተች?
ሦስቱ ጓደኛሞች የት ተገናኙ?
ጫጩት ያለቀሰችው ተደስታ ነው ወይስ አዝና?
ከሦስቱ ጓደኛሞች ልዩ የሆነው ማነው?

