ምክር ያስፈታል ከእሥር
CODE Ethiopia
Mekasha Haile

በአንድ ወቅት በሠፈራችን አንዲት ቆቅ ከልጇ ጋር ትኖር ነበር:: ከዕለታት አንድ ቀን የቆቅ ልጅ የስንዴ ሰብል አሽቶ ታያለች:: በእርሻው አጠገብም ወጥመድ እንደተጠመደበት አየች:: ይሄን የተመለከተችው የቆቅ ልጅ እናቷን "እናቴ ሆይ! የስንዴ እሸት አምሮኝ ነበር፤ ማሳው ውስጥ ገብቼ እንዳልበላ ወጥመድ ይይዘኛል፡፡

1

እናቷም ‹‹ተይ ልጄ፤ ይቅርብሽ፤ ትያዣለሽ፤ ይቅርብሽ፤ አይሆንም›› ብላ መከረቻት፡፡ ልጅቷ ግን ‹‹አይዘኝም፣ ትንሽ በላ በላ አድርጌ ልውጣ›› አለችና ማሳው ውስጥ ገብታ መብላት ጀመረች::

2

በልታ ከጠገበች በኋላ ለመውጣት ስትሞክር ወጥመዱ እግሯን አሥሮ ያዛት፡፡

3

መቼም መከራ በመጣ ጊዜ መጀመሪያ የሚታሰቡት ወላጆች ስለሆኑ ያቺ የእናቷን ምክር አልሰማ ያለች ልጅ "እናቴ ኧረ ተያዝኩልሸ" አለቻት:: እናትም "ምነው ልጄ አስቀድሜ ነግሬሽ አልነበረምን? አሁን ታዲያ ምን ላደርግልሽ እችላለሁ?" ስትል መለሰችላት፡፡

4

"እማምዬ እባክሽን ፍችልኝ?" አለች ልጅቷ፡፡
"በምን እጄ?" እናት መልሳ ጠየቀች፡፡
"ታዲያ እንዴት ልሁን? ምን ይበጀኝ? የኔ እናት!"
ብላ በጭንቀት ጠየቀች፡፡ በዚህ ጊዜ እናት ልጇን መካሪና አስተማሪ፤ ከክፉም ጠባቂ ናትና "ዝም ብለሽ የሞትሽ መስለሽ ተኚ! ባለወጥመዱ ሲመጣ ሞታለች ብሎ ፈትቶ ይለቅሻል፡፡ በዚያን ጊዜም ታመልጫለሽ፡፡" አለቻት፡፡ ልጅቷም እናቷ እንደመከረቻት አደረገች፡፡

5

ባለማሳው ሰውዬ ሰብሉን ጎብኝቶ ከጨረሰ በኋላ ወደ ወጥመዱ ሲመለከት ዝልፍልፍ ብላ ትንሿ ቆቅ እይኗን አጨልማ ተኝታ አያት፡፡

እርሱም የሞተች መሰለውና "አዬ ጉድ! ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበር፤ ነገር ግን በክታለች፡፡" በማለት አዘነ::

6

የሰውዬው ጓደኛ ከፍ ብሎ ባለው ማሳ ሰብሉን ይጠብቅ ነበርና "ወንድም!" ሲል ተጣራ፡፡ ቀጥሎም "ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በክታ አገኝኋት፡፡" አለው:: ባልጀራውም "እስቲ ወደ ላይ አጉናት!" አለው፡፡ እሱም "እያት" አለና ወደ ሰማይ ወርወር ሲያደርጋት ቱር ብላ ከጫካዋ ገባች ይባላል፡፡

7

ልጆች!
የወላጆችንም ሆነ የታላላቆችን ምክር በአግባቡ መስማት ተገቢ ነው፡፡ የወላጅን ምክር አለመስማት የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም ለተቸገረ ሰው አፋጣኝ ምላሽ ወይም ምከር መስጠት አስፈላጊ መሆኑ መገንዘብ ይገባል፡፡

8
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ምክር ያስፈታል ከእሥር
Author - CODE Ethiopia, Nema Behutiye
Illustration - Mekasha Haile
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs