ቅናት ዋጋ ያስከፍላል
CODE Ethiopia
Mekasha Haile

በድሮ ጊዜ በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ አለሚቱና አልማዝ የሚባሉ ሁለት ጎረቤታሞች ነበሩ፡፡

1

ሁለቱም ወንድ ልጆች ነበሯቸው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ አለሚቱ በአልማዝ ትቀና ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አልማዝ ትታመምና ሌላ ምግብ አልበላ ሲላት ልጇን ዳቦ እንዲገዛላት ወደ ሱቅ ትልከዋለች:: ጊዜው ምሽት ስለነበር ልጁ ሳይመለስ ጠፍቶ ይቀራል፡፡

2

አለሚቱም በህመሟ ላይ የልጇ መጥፋት ታክሎበት ብዙ ተንገላታች፡፡ ሆኖም ከረጅም ጊዜ በኋላ ታክማ ዳነች፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቤት ፍለጋ ጀመረች፡፡ በመንገድ ላይ አንድ ልጅ አገኘችና "እባክህ የእግዚአብሔርን ቤት አሳየኝ?" አለችው፡፡

3

ልጁም "ያቺን ፈረስ መልሽልኝና" አሳይሻለሁ ይላታል፡፡ እሷም እሺ ብላ ታቀብለዋለች፡፡ ካቀበለችው በኋላ "ያንን መሶብ የተሸከመውን ልጅ ጠይቂው፡፡" አላት፡፡

4

እሷም "አንተ ባለመሶብ እባክህ አምላክ ያለበትን አሣየኝ?" አለችው፡፡ "ይችን መሶብ እቤት አድርሽልኝና!" አላት፡፡

5

እሷም "እሺ!" ብላ አደረሰችለት፡፡ ካደረሰችለት በኋላም "ያንን ባለመደብር ጠይቂው፡፡" ይላታል፡፡ "እሺ!" ብላ ወደ ባለ መደብሩ ትሄድና "አንተ ባለመደብር እባክህ አምላክ ያለበትን አሣየኝ!" ስትለው "አንዴ ሱቄ ውስጥ ሆነሽ ሽጭልኝና" ይላታል፡፡ እርሷም "እሺ!" ብላ ወደ ውስጥ ገብታ ትሸጥለታለች፡፡

6

ባለሱቁም በበኩሉ "ያችን የልጆች እናት ጠይቂ" ይላታል፡፡ በዚሁ ተስማምታ ሴትዮዋን ስትጠይቃትም "በመጀመሪያ የልጆቼን ገላ እጠቢልኝ፡፡" ትላታለች፡፡ እሺ ብላ ካጠበችላት በኋላ "አምላክ በየትኛውም ቦታ ይገኛል፡፡" ትላታለች፡፡

7

ሴትዮዋም ባለችበት ተምበርክካ እያለቀሰች"ልጄን ጅብ ስለበላብኝ ልጅ ስጠኝ፡፡" አለችው፡፡ አምላክም "ወደ ቤትሽ ተመለሺና ዳቦ ጋግረሽ፣ ጎረቤትሽን ጠርተሽ፣ መሶብሽን ክፈችው" አላት፡፡ ከዚያም እንዳላት አድርጋ መሶቧን ከፍት ስታደርግ ከበፊቱ የበለጠ የሚያምር ልጅ አገኘች፡፡

8

አለሚቱ በአልማዝ ዕድል በጣም ቀናች፡፡ እሷም እንደ አልማዝ ለመሆን አስባ ልጇን ሳትቸገር ስኳር ግዛ ብላ በማታ ወደ ሱቅ ላከችው፡፡ ልጇም ሰኳር ሊገዛ በሄደበት ምሽት በጅብ ተበላ፡፡

9

እንደ አልማዝ አምላክን ፍለጋ ጀመረች፡፡ በመንገዷም አንድ ባለፈረስ አገኘች፡፡ "አንተ ባለፈረስ የአምላክን ቤት አሣየኝ" አለችው፡፡ "ፈረሴን ምግብ አብዪኝና አሳይሻለሁ፡፡" አላት፡፡

10

"ያንተን ፈረስ ቀላቢ ነኝ?" አለችው፡፡ እሱም "ያንን መሶብ የተሸከመውን ልጅ ጠይቂው፡፡" አላት፡፡ "አንተ ባለመሶብ አምላክን ቤት አሣየኝ፡፡" አለችው:: "ይህንን መሶብ እቤቴ አድርሽልኝና!" አላት፡፡

11

"እኔ የአንተ መሶብ አድራሽ ነኝ?" አለችው፡፡ እሺ "ያንን ባለመደበር ጠይቂው፡፡" "አንተ ባለመደብር የአምላክን ቤት አሳየኝ አለችው፡፡" መጽሐፍ ሽጭልኝና አላት፡፡" "እኔ የአንተን መጸሐፍ ሻጭ ነኝ?" አለችው፡፡

12

እሱም እሺ "ያችን የልጆች እናት ጠይቂያት" አላት፡፡ "አንቺ ሴትዮ የአምላክን ቤት አሣይኝ፡፡" ብላ ጠየቀቻት ሴትዮዋም‹‹የልጄን ገላ እጠቢልኝና›› አለቻት፡፡

13

"እኔ የአንች ልጅ ገላ አጣቢ ነኝ?" አለቻት:: እሺ "ይሄውልሽ የአምላክ ቤት በዚያ በኩል ነው፡፡" አለቻት፡፡ ከዚያም ሰይጣንን አገኘችው፡፡ተንበርክካም "አምላኬ ሆይ ልጄን ጅብ ስለበላብኝ ልጅ ስጠኝ::" አለችው፡፡ እሱም "ቤትሽ ሣትገቢ ደጅሽ ላይ ጉድጓድ ቆፍሪ፡፡ ከዚያ ልጅሽን ታገኛለሽ፡፡" አላት፡፡ "እሺ!" ብላ ወደቤቷ ተመልሳ ወደ ውስጥ ሣትገባ ከቤቱ ፊት ለፊት ጉድጓድ ስትቆፍር አዞ አገኘች፡፡

14

አዞው ሊበላት ሲያባርራት ከአንድ ቤት በር ላይ አንድ አይጥ አየች፡፡ "አንተ አይጥ ደብቀኝ፡፡" አለችው፡፡ "ምኔ ትሆኛለሽ?" ሲላት "ሚስትህ!" አለችው፡፡

15

እሺ ይልና ዳዋ ውስጥ ይደብቃታል፡፡ ከዚያም አዞ መጣና "አቶ አይጥ አንዲት ሴት በዚህ በኩል አላለፈችም?" አለው፡፡ "አላለፈችም!" አለ አይጥ፡፡ አዞውም ሮጦ ወደ ጉድጓዱ ገባ፡፡ አይጥም "በይ ከዳዋው ውስጥ ውጪ፡፡ እኔ ጌሾና ባቄላ ከሰው ቤት አመጣለሁ፤ ለእንግዶች የሚሆን ጠላ ጥመቂ" አላት፡፡ "እሺ!" ስትለው ሁለት ፍሬ ባቄላና አንድ እግር ጌሾ አመጣላት፡፡ ጌሾውን ወቅጣ ብቅልና ትንሽ አሻሮ አዘጋጅታ ጠላ ጠመቀች፡፡

16

ባቄላውንም ቀቀለችና ጨው እንዳለው ለማረጋገጥ አንድ ፍሬ ባቄላ በላች፡፡ ከዛ ስለጣማት አንዷንም ፍሬ ደገመቻት፡፡ ሲያንቃት ጠላውን ጠጣችበት፡፡ አይጥ እንግዳዎቹን ይዞ ሲመጣ በቤቱ ውስጥ ምንም ነገር የለም፡፡ በዚህ ጊዜ በጣም ተናዶ በር ላይ ሲቀመጥ ከየት መጣ ሳይባል አሞራ ይዞት ሰማይ ላይ ወጣ፡፡ አሞራው አይጡን በመያዝ ወደ ላይ ሲበር ተሳስቶ በክንፉ የአለሚቱን ዓይን መታው፡፡ በዚያው ቅጽበት አይጡ ከጭልፊቱ አፍ አምልጦ በመውደቁ ሮጦ ጉድጓዱ ውስጥ ገባ በዚህም ሁኔታ የተነሳ አለሚቱ ቅናት ጎጂ እንደሆነ ተገነዘበች ይባላል::

17
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ቅናት ዋጋ ያስከፍላል
Author - CODE Ethiopia, Nema Behutiye
Illustration - Mekasha Haile
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs