

የቅድመ-ንባብ ጥያቄዎች
የምታውቋቸውን የዱር እንስሳት ስም ጥቀሱ?
የምትጫወቱትን ጨወታ ሕግና ደንብ ታውቃላችሁ?
ተስማምቶ መጫወት ለምን ይጠቅማል?
• መጣላት ምንን ያስከትላል?
በአንድ አካባቢ ጦጢት፣ አያ አንበሶ፣ ቀጭኔና የሜዳ አህያ በአንድ ላይ ይኖሩ ነበር፡፡ ሁሉም የሚተዳደሩት በግብርና ስራ ነበር፡፡
ጦጢት ፍሬያቸው የሚበላ እንደ አጋም፣ እንጆሪና ኮሽም ያሉ አትክልቶችን ታለማለች፡፡
አያ አንበሶ እንደ ሚዳቋ፣ ድኩላና የሜዳ ፍየል ያሉ የሥጋ እንስሳትን ያረባል፡፡
ቀጭኔ እንደ ግራር ያሉ ረጃጅም ዛፎችን ተክሎ ይንከባከባል፡፡
የሜዳ አህያ ግን ምንም ሳይሠራ በራሱ ክልል ያለውን ሣር እየጋጠ ይኖራል፡ ሲጠግብም ይተኛል፡፡
እንስሳቱ አንዱ የሌላውን ድንበር ሳይጥስ ተከባብረው ለመኖር ተስማሙ፡፡ የየራሳቸውን ክልልም በአጥር አጠሩ ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሜዳ አህያ በራሱ ክልል የነበረው ሣር አለቀበት፡፡ የሚበላው ስላጣ በጣም ተራበ፡፡
አንድ ቀን ረሃቡ ጠናበት፡፡ ስለሆነም የጦጢትን አጥር ሰብሮ ገባ፡፡ ከአትክልቷ ውስጥ ለምለም ሣር ሲግጥ ጦጢት ደረሰችበት፡፡
"የምበላው ሣር አጥቼ ስለራበኝ ነው፤ እባክሽን ይቅርታ አድርጊልኝ?" አላት፡፡
"ከራበህ ታዲያ ለምን አስቀድመህ አትጠይቀኝም?" አለችው፡፡
የሜዳ አህያውም "አንቺ የምትኖሪው ዛፍ ላይ፤ የምትበዪው የዛፍ ፍሬ፤ ምን ይሁን ብዬ ነው ለተፈጥሮ ሣር ፈቃድ የምጠይቅሽ?" አላት፡፡
ጦጢትም "አቅም የላትም፣ ምንም አታደርገኝም፣ ብለህ አይደለም መብቴን የደፈርከው? ነግሬሃለሁ፤ ሁለተኛ ወደ ግቢዬ እንዳትመለስ" አለችው፡፡
የሜዳ አህያውም በጣም ተናዶ "ይህች በረሮ እስቲ የምታደርገኝን አያለሁ" በማለት በማግስቱም ተመለሰ፡፡
ጦጢት ሌሊቱን ጉድጓድ ቆፍራ ቅጠል አልብሳው አደረች፡፡ የሜዳ አህያው በለመደው መንገድ ሲገባ ጉድጓዱ ውስጥ ገብቶ ወገቡ ተሰበረ፡፡ በትዕቢቱ ጉዳት አተረፈ፡፡
ጦጢትም አህያው በጀርባው ተንጋሎ ስታይ፣ "እንደሌሎቹ ጉልበት ኖሮኝ ባልፈራም ላንተ የሚሆን ብልሀት አላጣም" አለችው ይባላል፡፡

