

በዱሮ ጊዜ እናቱን በጣም የሚወድ አንድ አንበሳ ነበር አሉ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን የሚወዳት እናቱ በጠና ትታመማለች፡፡ ብዙ
ጊዜ ቢያስታምማትም አልተሻላትም:: ጭንቋን ማየት ስላልቻለ አራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ "እናቴ በጣም ታማለች፡፡ ብዙ ደክሜ አስታመምኳት፤ ግን ምንም አልተሻላትም፤ ስለዚህ ቁጭ ብዬ ስቃይዋን ማየት አልፈልግም፡፡
ቀጥሎም "ርቄ እሄዳለሁ፡፡ መሞቷንም መዳኗንም እንዳትነግሩኝ፡፡ የነገረኝን ገድዬ እጥለዋለሁ፡፡" ብሎ ጫካ ውስጥ ይገባል፡፡
ምድረ-አራዊትም በየተራ እያደረ የአንበሳውን እናት መጠበቅ ጀመረ፡፡ ከዚያም ሞት አይቀርምና የአንበሳው እናት ሞተች፡፡ ለአያ አንበሶ ማን ያርዳው? ሁሉም ፈሩ፤ ከዚያ ሁሉ አራዊት መካከል "እኔ አረዳዋለሁ፡፡ ምን ትሰጡኛላችሁ?"ስትል ቀበሮ ጠየቀች፡፡ አራዊቱም ከተማከሩ በኋላ "አንቺ መርዶውን ነግረሽው መጠቶ እናቱን ከቀበረ እድሜሽን ሙሉ ዶሮና የበግ ግልገል እንድትበይ እንመርቅሻለን፡፡"አሏት፡፡
ቀበሮም በዚህ ተስማምታ ግማሽ ራሷን ተላጭታ፣ ግማሹን ደግሞ ጎፈሬ አድርጋ በደንብ አበጠረች፡፡
ከዚያም ወደ ጫካው በመሄድ አንበሳውን አገኘችው፡፡ አንበሳም ገና ሲያያት "የእናቴን ሞት ልታረጅኝ ወይም መዳኗን ልትነግሪኝ ከሆነ ወዮልሽ!" ይላታል:: እሷም "እናትህ ብትሞት እንዲህ ፀጉሬን አበጥራለሁ? ደግሞስ! እናትህ ብትድን እንደዚህ እላጫለሁ?"ብላ ጠየቀችው፡፡
ቀጥላም "ለማንኛውም ናና የሆነውን በዓይንህ እይ፡፡"ብላ እየመራች ወሰደችው፡፡ ከዚያም እናቱን አልቅሶ ከቀበረ በኋላ ወደ አራዊቱ ዞር ብሎ "እናንተ ለመንገር የፈራችሁትን ቀበሮ ደፍራ የነገረችኝ ስለሆነ ከእናንተ ይልቅ እርሷ ምስጋና ይገባታል፡፡"ብሎ አሞካሻት ይባላል፡፡ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ይባል የለ!

