በቅሎዋ ዋርዲት
Mesfin Habte-Mariam
Marleen Visser

ከእለታት አንድ ቀን ዋርዲት የምትባል አንዲት በቅሎ ነበረች፡፡ ቆንጆ፣ በጣም ጎበዝና ኩሩም ነበረች፡፡ አንድ ቀን ዋርዲት ውሃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ እየወረደች ነበር፡፡

1

አንድ ቆንጆ ወጣት ፈረስም በተመሳሳይ መንገድ ላይ እየሄደ ነበር፡፡ ፈረሱም ዋርዲትን ስላያት እንዲህ አሰበ፡፡ ''ከዓለም በጣም ቆንጆዋ በቅሎ ይቻት! እሷን ማግባት አለብኝ፡፡''

2

''ወዴት እየሄድሽ ነው?'' በማለት ፈረሱ ዋርዲትን ጠየቃት፡፡ ''ውሃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ እየወረድኩ ነው'' ስትል መለሰችለት፡፡ ፈረሱም ''አብሬሽ ልሂድ'' አላት፡፡.

3

ፈረሱ ''ዋርዲት አንቺ እኮ ከዓለም እጅግ ቆንጆዋ በቅሎ ነሽ! እባክሽ ላግባሽ!'' አላት፡፡ ዋርዲት ፈረሱን አየችው፡፡ ''ልጅ እግር፣ ቆንጆና ጎበዝ ነው፡፡ አዎ አገባዋለሁ!'' ስትል አሰበች፡፡

4

ፈረሱም ስለወደፊት ሚስቱ ሁሉን ነገር ለማወቅ ፈለገ፡፡ ''አባትሽ ማነው? እናትሽስ ማነች?'' ሲል ጠየቃት፡፡ ዋርዲትም አንገቷን ዘወር አደረገች፡፡ ልትመልስለት አልፈለገችም፡፡ ''የኔ ውድ'' አለ ፈረሱ፡፡ ''የሙሽራዬን ቤተሰብ እኮ ማወቅ አለብኝ፡፡''

5

ዋርዲት ሳቀች፡፡ ''እናቴን በየቀኑ ታያታለህ፡፡ ቤተመንግሥት ነው ያለችው፡፡ አገረ-ገዢው በየማለዳው ይጋልባታል፡፡ ''አባትሽስ ማነው?'' በማለት ፈረሱ ጠየቃት፡፡

6

''እህቴ የቄሱ ንብረት ነች፡፡ አታውቃትም እንዴ? ወደ ቤተክርስቲያን ጋልበዋት ይሄዳሉ'' አለችው ዋርዲት፡፡ ''እሺ፣ አባትሽስ ማነው? የት ነው?'' ሲል ጠየቀ ፈረሱ፡፡.

7

ዋርዲትም ንግግሯን ቀጠለች፡፡ ''አክስቴ ደግሞ በጣም ቆንጆ ነች! ከሰፈሩ አለቃ ጋር ነው የምትኖረው፡፡ እንደ ልጁ ነው የሚወዳት፡፡ ''ከሆነ ጥሩ ነገር ነው'' አላት ፈረሱ፡፡ ''ግን በኔ ሞት፣ ስላባትሽ ንገሪኝ፡፡''

8

ወዲያውኑም አንድ አሮጌ አህያ በመንገዱ ቁልቁል መጣ፡፡ የዋርዲት አባት ነበር፡፡ አየት አድርጋው አፈረችበት፡፡ ''አባቴ አህያ ነው'' ስትል አሰበች፡፡ ፈረሱ ደግሞ አህያ አማቱ እንዲሆን አይሻም፡፡

9

አህያው ወደ ዋርዲት ቀረብ አለ፡፡ እንኳን ሰላም ልትለው ቀርቶ በዓይኗም አላየችውም፡፡

10

''ዋርዲትዬ'' አላት አሮጌው አህያ፡፡ ''ምን ሆንሽብኝ ልጄ?'' በማለት ጠየቃት፡፡ ''ምን ሆነሽ ነው የማታናግሪኝ?'' አላት በልጁ ስለተናደደባት፡፡ ዋርዲት ግን ቃል አልተነፈሰችም፡፡ ወደ ሌላ አቅጣጫ ዞራ አየች፡፡.

11

ፈረሱ ተናደደ፡፡ ''ይህ ጅላጅል አሮጌ አህያ ማነው? ለምንድነው የሚያናግርሽ?'' ሲላት፤ ''አላውቀውም'' አለች ዋርዲት፡፡

12

''አታውቂኝም? ዋርዲት፣ እኔ እኮ'' አለቀሰ አሮጌው አህያ፡፡ ፈረሱ ግን እያደመጠ አልነበረም፡፡.

13

''ሂድልኝ'' በማለት ጮኸ ፈረሱ፡፡ ''አንተ ቂል አሮጌ አህያ! ዘወር በል!'' አሮጌው አህያ ፈቅ አላለም፡፡ ፈረሱ በእርግጫ ሲመታው አህያው ወደቀ፡፡.

14

አህያው ሰማይ ሰማይ እያየ ''አምላኬ፣ ይህንን ጉድ አየህልኝ?'' እያለ አለቀሰ፡፡ ያ አሮጌ አህያ ልቡ ተሰንጥቃ ሞተ፡፡

15

ፈጣሪም የአህያውን ለቅሶ አይቶ ለዋርዲት እንዲህ አላት፡፡ ''ዋርዲት፣ አባትሽ ሞቷል፡፡ በመሆኑም አንቺን መቅጣት አለብኝ፡፡ ፈረሶች ልጅ ይውለዱ ፤ አህዮችም ይውለዱ፡፡ አንቺ ግን ልጅ በዓይንሽ አታዪም፡፡ አባትሽን ስላላከበርሽ ቅጣትሽ ይህ ነው፡፡

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
በቅሎዋ ዋርዲት
Author - Mesfin Habte-Mariam, Elizabeth Laird
Translation - መዘምር ግርማ
Illustration - Marleen Visser
Language - Amharic
Level - First paragraphs