ውለታ የማይረሱት እንስሳት
Mariam Mohammed
Rob Owen

ከዕለታት በአንዱ አንድ ሰውዬና አምስት እንስሳት ወደ ጦርነት እየሄዱ ነበር፡፡ ፀሐይ እስክትጠልቅም ድረስ አብረው ተጓዙ፡፡ ''የት ነው የምናድረው?'' ስትል አህያ ጠየቀች፡፡ ''እዩ፣ እዚያ ማዶ ጎጆ ቤት ይታየኛል፤ እዚያ እናድራለን''አለ እባቡ፡፡

1

ወደ ጎጆውም ሄደው ተጣሩ፡፡ አንዲት ሴትዮና አንድ ሰውዬም ብቅ አሉ፡፡ ''ኑ ግቡ እዚህ እደሩ፤ የምንመግባችሁ ምግብ ግን የለንም'' አላቸው ሰውየው፡፡ ''ከቤታችሁ ውጪ ያለችውስ ላም?'' ሲል ውሻው ጠየቀ፡፡ ''ያለችን ብቸኛ ሀብት እሷው ነች እኮ!'' አለች ሚስትዮዋ፡፡ ''ካረድናት ምን ይቀረናል?'' እንግዳው ሰውዬ ደግሞ ''ውለታችሁን አንረሳም'' አላቸው፡፡ ''እባካችሁ እሷን እረዱልን፡፡''

2

''ደሟን ከሰጣችሁኝ፤ ባለውለታችሁ እሆናለሁ'' አለ አንበሣው፡፡ ''አጥንቷን ብትሰጡኝ ይቺን ደግነታችሁን ሳስታውሳት እኖራለሁ'' አለ ውሻው፡፡ ''ጮማውን ብትሰጡኝ ብድር ይገባችኋል'' አለ እባቡ ደግሞ፡፡ ንሥር ደግሞ ''ከቆዳዋ ስር ያለውን ስጋ እፈልጋለሁ፡፡ እባካችሁ'' አላቸው፡፡ ''ለኔ ወተቷን'' አላቸው ሰውዬው፡ ''አንድ ቀን ድንቅ የሆነ ነገር አደርግላችኋለሁ፡፡'' ''ሥጋ አልፈልግም፡፡ ትንሽ ሳር ከጣራችሁ ላይ ስጡኝ'' አለች አህያዋ፡፡.

3

ባልና ሚስቱ ላማቸውን አረዷት፡፡ ደሟን ለአንበሣው ሰጡት፡፡ አጥንቷን ለውሻው፣ ወተቱን ለሰውየው፣ ጮማውን ለእባቡ፣ ከቆዳዋ ስር ያለውን ሥጋ ለንሥር አከፋፈሏቸው፡፡ ለአህያም ከጣራው ስር ሳር ተመዞ ተሰጣት፡፡

4

መንገደኞቹ ያንን ምሽት በደህና አሳለፉና በማግስቱ ማልደው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡

5

ብዙ ሳምንታት አለፉ፡፡ ከዚያም አንድ ቀን ሰውዬውና ሚስቱ አንድ አንበሣ በጎጇቸው አቅራቢያ ሲያገሣ ሰሙት፡፡ ውጪ ላይ ነበሩ፡፡ አንበሣው ግን እዚያ አልነበረም፡፡ ትልቅ የዝሆን ቀንድ ግን መሬት ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ''ይህ ቀንድ ትልቅ ዋጋ ያለው ነው'' አለች ሴትዮዋ ለባሏ፡፡ ''ወደ ቤት ውሰጂው'' አላት ባሏ፡፡ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ምን አልባት እኮ ሌባ መጥቶ ሊሰርቀን ይችላል፡፡''

6

ወዲያውኑም ውሻ ጮኸ፡፡ ባልና ሚስቱም ወደኋላቸው አዩ፡፡ ውሻው በራቸው አቅራቢያ ነበር የተኛው፡፡ ''አይዟችሁ'' አላቸው፡፡ ''እኔ ሌቦችን እጠብቃለሁ፡፡ እናንተ አንድ ጊዜ ስላገዛችሁኝ እኔም አሁን አግዛችኋለሁ፡፡''

7

ባልየው ክፉ ወንድም ነበረው፡፡ ወንድምዬው ሀብታምና ክፉ ነበር፤ ሰው ሁሉ ይጠላዋል፡፡ ይህ ወንድሙ ስለ ዝሆን ቀንዱ ሰማ፡፡ ''ቀንዱን እፈልገዋለሁ'' በማለት አሰበ፡፡ ''ወንድሜን ገድዬ እወስደዋለሁ፡፡''

8

ሌሊት ላይ ወደ ወንድሙ ቤት ሄደ፡፡ እባቡ መንገዱ ላይ ተኝቶ እየጠበቀው ነበር፡፡ ክፉውን ወንድም ነደፈው፡፡ ወዲያውኑም ወንድምዬው ሞተ፡፡

9

በዚያች አገር ሰው ከሞተ ወንድሙ ሀብቱን ይወርሳል፡፡ ስለዚህ የክፉው ወንድም ላሞችና በጎች የባልና ሚስቱ ንብረት ሆኑ፡፡ ሰውየው ለሚስቱ ''አንበሣው፣ ውሻውና እባቡ ውለታቸውን ከፈሉን'' አላት፡፡ ''ንሥሯ፣ አህያዋና ሰውዬውስ ምን ያደርጉልን ይሆን?''

10

አንድ ቀን ንሥሩ በሰማይ ላይ ይበር ነበር፡፡ ቁልቁል ሲያይ በቡድን የሚሄዱ ሽማግሌዎችን አየ፡፡ ሽማግሌዎቹ የሚያብረቀርቅ ነገር ይዘው ነበር፡፡ ''ገንዘብና ጌጣጌጥ ይዘዋል'' ሲል አሰበ ንሥሩ፡፡ ''ከሚስት ለባል የሚሆን ስጦታ ይዘው እየሄዱ ነው፡፡ ለነገሩ ከባል ለሚስትም ይሆናል፡፡ ተጣልተው በዚህ ሊያስታርቋቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ ግን በዚህ ይታረቃሉ?''

11

ንሥር ተስፈንጥሮ ስጦታውን ከሽማግሌዎቹ እጅ ቀማና በባልና ሚስቱ ወዳጆቹ በር ላይ ጣለው፡፡

12

በዚሁ ቀን አህያ ብዙም በማይርቅ ጫካ ውስጥ ነበረች፡፡ በጀርባዋ የተሸከመችው በገንዘብ የተሞላ ሻንጣ ነበር፡፡ ጌታዋ ''ፈጠን ብለሽ ሂጂ፤ አንቺ ደደብ ሰነፍ ፍጥረት'' በማለት ይጮህባትና ይደበድባት ነበር፡፡ አህያዋ ይህን ክፉ ፍጥረት ለመቅጣት ፈለገች፡፡

13

አህያዋ ሮጠችና ወደ ሰውዬው እና ሴትዮዋ ጎጆ ሄደች፡፡ ''ይህን ገንዘብ ውሰዱት'' አለቻቸው፡፡ ''ለናንተው ነው ያመጣሁት፡፡'' ሰውየውና ሚስቱ አሁን በለጸጉ፡፡''

14

''ወዳጆቻችን እንስሶቹ አያሌ ውለታ ዋሉልን'' አለ ሰውየው፡፡ ''እንኳንም ላማችንን አረድንላቸው፡፡'' ሰውየው ግን ገና ውለታውን አልመለሰልንም'' አለች ሚስቱ፡፡ ''እንስሶቹ ብዙ ነገር አድርገውልናል፤ ሰውየው ግን በእርግጠኝነት የበለጠ ያደርግልናል፡፡''.

15

ቢጠብቁት ቢጠብቁት! ሳምንታት፣ ወራት፣ ዓመታት ቢያልፉም ሰውየው አልመጣም፡፡ እንስሶቹ ውለታቸውን አይረሱም፡፡ ሰዎች ግን ይረሳሉ፡፡

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ውለታ የማይረሱት እንስሳት
Author - Mariam Mohammed, Elizabeth Laird
Translation - መዘምር ግርማ
Illustration - Rob Owen
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs