የአይጦች ንጉሥ ልጅ
Merga Debelo
Salim Kasamba

አንድ በጣም ኩሩ የአይጦች ንጉሥ ነበር፡፡ ''አይጦች በዓለም ላይ ድንቅ እንስሳት ናቸው'' ይላል፡፡ ሁሉም ሌሎች አይጦች በንግግሩ ይስማማሉ፡፡ ''ልክ ነዎት'' ይሉታል ሁሉም በአንድ ድምጽ፡፡ ''በዓለም ላይ ድንቅ ፍጥረታት ነን፡፡''

1

''በዚህች ዓለም በጣም ደንቁ ንጉሥ እኔ ነኝ'' አለ የአይጦቹ ንጉሥ፡፡ ''ልክ ነዎት! በዓለም ላይ ወደር-የለሽ ንጉሥ ነዎት'' በማለት ሁሉም አይጦች ጮሁ፡፡

2

''ልጄ በዓለም ላይ አቻ የማይገኝለት ልዑል ነው'' አለ የአይጦቹ ንጉሥ፡፡ ''እንስማማለን! ልጅዎት በዓለም አቻ የማይገኝለት ልዑል ነው'' ሲሉ ሁሉም አይጦች ስምምነታቸውን ገለጹለት፡፡.

3

''ለልጄ ሚስት እንፈልግለት'' አለ የአይጦቹ ንጉሥ ለአዛውንቶቹ፡፡ ''አይጥን የሚስተካከል ሌላ ማንም እንስሳ የለም፡፡ ልጄ በዓለም አለች የተባለችውን ሴት ማግባት አለበት፡፡ ግን የት እናግኛት ያችን ልጅ?''.

4

አዛውንቶቹ ለረጅም ጊዜ አሰቡ፡፡ ከዚያም አንዳቸው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፣ ''ከኛ የሚበልጥ አንድ ሰው አለ፡፡'' ''ማነው በል?'' ሲል የአይጦቹ ንጉሥ ጠየቃቸው፡፡ ''ፈጣሪያችን ነው'' አሉ ሽማግሌው፡፡ ''ልክ ብለዋል'' አለ ንጉሡ፡፡ ''ፈጣሪያችን ከኛ በላይ ነው፡፡ ሂዱና ልጅህን ዳርልን በሉት፡፡''

5

አዛውንቶቹ አይጦች ወደ ሰማይ ፈጣሪያቸውን ለማግኘት ሄዱ፡፡ ''እባክህ'' በማለት ጀመሩ፡፡ ''የንጉሣችን ልጅ የሆነው ልዑላችን በዓለም ድንቅ የተባለ ፍጥረት ነው፡፡ ልጅህን ብትድርልን ብለን ነው አመጣጣችን፡፡

6

ፈጣሪም ፈገግ አለና ''እውነት ልዑላችሁ ከዓለም ሁሉ ድንቅ ፍጥረት ከሆነ ለልጄ በጣም ይበዛባታል፡፡ ከሷ የበለጠች ማግባት አለበት'' አለ ፈጣሪ፡፡ ''ማነች ከሷ የምትበልጠው?'' ሲሉ አይጦቹ ጠየቁት፡፡ ''እንቁራሪት ከኔ በላይ ነው'' አለ ፈጣሪ፡፡ ''እንቁራሪት ሰማይ ድረስ መጥቶ ይሸፍነኛል፡፡ ከሱ ማምለጥ አልችልም፡፡ ላባርረው አልችልም፡፡ እሱን ሂዱና ልጅህን ዳርልን በሉት፡፡

7

አዛውንቶቹም ወደ ንጉሣቸው ሄዱ፡፡ ''ፈጣሪ ሁልጊዜም ትክክል ነው'' አለ የአይጦቹ ንጉሥ፡፡ ''እንቁራሪት ይበልጠዋል፡፡ ሂዱና እንቁራሪትን ልጅህን ለልጃችን በሉት፡፡''

8

በዚህም መሰረት ሽማግሌዎቹ ወደ እንቁራሪቱ ሄዱ፡፡ ''ልዑላችን ከዓለም እንስሳት ሁሉ ታላቁ ነው፡፡ ልጅህን ለማግባት ይፈልጋል'' አሉት፡፡ ''እስኪ ትንሽ ስለሱ ንገሩኝ'' አለ እንቁራሪቱ፡፡ ''ጎበዝ ነው፤ ቆንጆም ነው'' ሲሉ ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ ''በቃችሁ!'' አላቸው እንቁራሪቱ፡፡ ''ለልጄ በጣም ይበዛባታል፡፡ ከኔ ከሚበልጥ ጋር መጋባት አለበት'' አላቸው፡፡

9

''ከእንቁራሪት ደግሞ የሚበልጥ ማነው?'' ሲሉ ሽማግሌዎቹ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ''ነፋስ ትበልጠኛለች'' አለ እንቁራሪቱ፡፡ ''አሽቀንጥራ ነው የምትጥለኝ፡፡ ጭራሽ አልቋቋማትም እኮ፡፡ በሉ ልጅሽን ዳሪልን በሏት'' ሲል ምክሩን ለገሳቸው፡፡.

10

ሽማግሌዎቹ ወደ አይጦቹ ንጉሥ ሄዱ፡፡ ''አይ አንቁራሪት! ልክ ነው እኮ'' አለ ንጉሣቸው፡፡ ''ንፋስ እውነትም ከሱ ታይላለች፡፡ በሉ ሂዱና ልጅሽን ዳሪልን በሏት'' አላቸው፡፡

11

ሽማግሌዎቹም ንፋስን ለማግኘት ሄዱ፡፡ ''ታላቋ ንፋስ ሆይ'' በማለት ጀመሩ፡፡ ''ከአይጦች ንጉሥ ተልከን ነው አመጣጣችን፡፡ ከዓለም ታላቁ ንጉሥ ሲሆን፤ ልጅሽ ልጁን እንድታገባ ይፈልጋል'' ''በእውነት የዓለም ሁሉ ታላቅ ንጉሥ ነው?'' ስትል ንፋስ ጠየቀች፡፡ ''ለልጄ እጅግ ሲበዛባት ነው፡፡ ልዑላችሁ ሌላ የበለጠ መፈለግ አለበት'' አለቻቸው፡፡

12

''ከንፋስ ደግሞ የሚበልጥ ማነው?'' በማለት ሽማግሌዎቹ ጠየቁ፡፡ ''ተራራ ይበልጠኛል'' ሲል ንፋስ መለሰላቸው፡፡ ''ወደሱ ስንትና ስንት ጊዜ እነፍሳለሁ፤ ግን ንቅንቅ አይልልኝም፡፡ ሂዱና ተራራን ልጅህን ዳርልን በሉት፡፡'' አዛውንቶቹም ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡ ''አዎን!'' ሲል ጮኸ፡፡ ''ንፋስ አልተሳሳተም፡፡ በሉ ሂዱና ተራራውን አናግሩት፡፡''.

13

በመሆኑም አዛውንቶቹ ሄደው ተራራውን አናገሩት፡፡ ''እንደምትሉት ልዑላችሁ ሃይለኛና ታላቅ ነው?'' ሲል ተራራ ጠየቃቸው፡፡ ''ከሆነማ ለልጄ ይበዛባታል፡፡ ከሷ የበለጠችውን ማግባት አለበት'' ''ማነች? ማነች?'' ሲሉ አዛውንቶቹ ጠየቁ፡፡ ''የዱር አይጥ ከኔ ይበልጣል'' አላቸው ተራራው፡፡   ''እኔን እየቦረቦረ ጎሬ ሲሰራ መቼ አስቆመዋሁ?''

14

አዛውንቶቹ ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡ ንጉሣቸውም ''የዱር አይጡ! አይጠመጎጥ? ወዳጄ እኮ ነው፡፡ ልጁ ለልጄ ጥሩ ሚስት ትሆነዋለች፡፡''

15

ልዑሉ አይጥም የአይጠመጎጥን ልጅ አገባ፡፡ ለብዙ ዓመታም በደስታ ኖሩ፡፡

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
የአይጦች ንጉሥ ልጅ
Author - Merga Debelo, Elizabeth Laird
Translation - መዘምር ግርማ
Illustration - Salim Kasamba
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs